የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ፣ ከ2010 ዓ.ም. ለውጥ በኋላም ሆነ በፊት በዘውግ (ብሔር) ማንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ሒደት፣ የአገሪቱን ዕድገትና ዴሞክራሲ ወደ ኋላ ያስቀረና ዕልባት ያላገኘ ከመሆኑም ሌላ፣ ለዜጎች መፈናቀል፣ ሞትና ሰላም ማጣት መንስዔ ሆኖ መቀጠሉን ተናገረ፡፡

ኢዜማ ይህን የተናገረው የፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቢሾፍቱ ከተማ ከየካቲት 22 እስከ የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ለሦስት ቀናት ባደረገው ስብሰባ፣ በድርጅቱ አሠራር ሒደትና ወቅታዊ አገራዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ፣ እንዲሁም በቀጣይ ስለሚኖሩ ድርጅታዊ ተግባራት ላይ ተወያይቶ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ትናንት የካቲት 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫው ነው፡፡

ፓርቲው በመግለጫው እንዳስታወቀው፣ ላለፉት 30 ዓመታት በተለይ በዘውግ ማንነት ላይ የተንጠለጠለው የፖለቲካ አስተሳሰብና መዋቅር እስካሁን አገራዊ አንድነቱን በማላላትም ሆነ ለዘላቂ አገራዊ ጥቅም ሥጋት ለሆኑ አያሌ ችግሮች ያጋለጠ መሆኑ ሳያንስ ‹‹በዚህ የተሳሳተ አስተሳሰብ የተለከፉ ኃይሎች ከባዕዳን ጋር ሳይቀር በመሠለፍ ብሔራዊ ጥቅሞችን አደጋ ላይ የሚጥሉ እንቅስቃሴዎቻቸውን›› በጥንቃቄ እየተከታተልኩ ነው ብሏል፡፡

ይሁንና እነዚህ ኃይሎች የትኞቹ ናቸው? የሚለው በመግለጫው ላይ በግልጽ አልተቀመጠም፡፡

ፓርቲው አያይዞም በኢትዮጵያ ወስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች ምንም እንኳን የተለያየ አመለካከትና ፍላጎቶች እንዳላቸው ቢያምንም፣ ‹‹የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚፈታተኑና የሕዝብን ሰላም የሚነሱ ጉዳዮች ሲከሰቱ ግን ከሁሉም አገር ወዳድ  ኃይሎች ጋር በጋራ እቆማለሁ፤›› ብሏል፡፡

ፓርቲው ለሦስት ቀናት ባደረገው ውይይትም ‹‹በልዩ ትኩረት ከታዩት ጉዳዮች መካከል፣ አገሪቱ ያለችበት ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ አንዱ ሲሆን፣ ውስጣዊ የፀጥታ ችግሮች፣ የኑሮ ውድነትና ቀጣናዊ ጉዳዮችን በየፈርጁ ተመልክቶ፣ አሁናዊና አገራዊ ፖለቲካው ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ ሁኔታ እየተለወጠ መምጣቱን ተገንዝቤያለሁ፤›› ብሏል፡፡

ኢዜማ በዚሁ መግለጫው ላይ እንዳብራራው፣ በአገሪቱ ባሉት የሰላም መታጣት፣ መፈናቀልና ሞት እንዲሁም በጂኦ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ምክንያት፣ ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች ነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ባለመቻሉ፣ ሕዝቡ በከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ ገብቷል ሲል ገልጿል፡፡

 ‹‹ማኅበረሰቡን ግራ ከመጋባት በማውጣት ሁሉም ዜጋ በእኩልነት የሚኖርባትን አገር ለመፍጠር የሚያስችል የፖለቲካ ሥርዓት ለመዘርጋት ይቻል ዘንድ፣ ፓርቲው ተለዋዋጭ የሆነውን የፖለቲካ ሥርዓት በተረዳ መልኩ ለሕዝቡ ጠንካራ የፖለቲካ አማራጭ ሆኖ ሊሠራ እንደሚገባ መግባባት ላይ እንደተደረሰም›› በመግለጫው አክሏል፡፡

ወቅቱን የሚመጥን የፖለቲካ አስተሳሰብና አሠራር ለማስፈን ይረዳ ዘንድም የአጭርና የረዥም ጊዜ ተግባራት ለይቻለሁ ያለው ኢዜማ፣ ይህንንም አስመልክቶ ‹‹በቅርቡ የተብራራ ሰነድ ይፋ እንደሚያደረግ›› አሳውቋል፡፡

የአገሪቱ ዜጎች በበርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች የተከበቡ ቢሆኑም እንኳን ‹‹የፖለቲካ ሥልጣን ማግኛ ብቸኛው መንገድ በሐሳብ ፉክክር ላይ የተመሠረተ ነፃና ገለልተኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ብቻ መሆኑ ላይም አቋሜ የማይናወጽ ነው፡፡ ለዚህም አበክሬ እሠራለሁ፤›› ሲልም አስታውቋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም አሁናዊ አገራዊ ፖለቲካ ላይ ፓርቲው እንደ አንድ ዋነኛ ባለድርሻ የሚጠበቅበትን ገንቢ ሚና ለመጫወት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊደረጉ ከሚገባቸው ፖለቲካዊ ተሳትፎዎች መካከል፣ በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ መቅረብ አንዱ ዕቅዱ መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህንንም ማሳካት እንዲያስችለው በቅርቡ በፓርቲው መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የሚመራ የምርጫ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰይሞ ወደ ሥራ ይገባል ብሏል፡፡