Ethiopian News

Ethiopian News
 • “ረሃብ ትችላለህን” ቢሉት፤ “ኧረ ጥጋብም እችላለሁ” አለ

  ከለታት አንድ ቀን በትልቅነታቸው የተከበሩ፣ በየጊዜው በሚካሄዱ ጦርነቶች ድል በማድረጋቸው የተፈሩ፣ አንድ የድሮ ጊዜ ንጉሥ ነበሩ፡፡
  ንግሥቲቱም እንደዚሁ፤ ንጉሡን በምክርም በማገዝ፤ በዘመቻ ጊዜ ስንቅ በማዘጋጀትም የመኳንንቱንና የመሳፍንቱን ሚስቶች አስተባብሮ በመምራትም በዙፋኑ ዙሪያ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ነበሩ፡፡
  ንጉሡና ንግስቲቱም በመዝናኛ በጨዋታ ጊዜያቸው፣ ወግ እየጠረቀ የግጥም ቃል እያዋጣ፣ ፈገግ ፈገግ የሚያሰኙ ቀልዶች አሰማምሮ በማቅረብ የሚታወቅ የንጉሥ አጫዋች ነበር፡፡ ንጉሡ ይጭኑት አጋሠስ፣ ይለጉሙት ፈረስ፣ ያጋጤቡት ወርቅ፣ ያስጥሉት ጠጅ፣ ያስጠምቁት ጠላ፣ የተትረፈረፋቸው ቢሆንም መንፈሳዊ ሃሴትን ይጉናፀፉ ዘንድ፣ ያ የንጉሥ አጫዋች ከምንም የሚበልጥባቸው ነውና እንደ አይናቸው ብሌን ይንከባከቡት ነበር፡፡ አንድ ቀን እንደተለመደው ግብር ገብቶ፣ ሰው ሁሉ በልቶ ጠጥቶ ከተሸኘ በኋላ፣ ልዩ አስተያየት የሚደረግላቸው የተባሉ የቅርብ የቅርብ ሰዎች ማለትም መኳንንቱና መሳፍንቱ እንዲሁም ባለሥልጣናቱ ልዩ መስተንግዶ ተደርጐላቸው በሉ ጠጡ፤ ተዝናኑ፤ ወደየማደሪያቸውም ተሸኙ፡፡
  እነሆ የንጉሡና የንግሥቲቱ ማረፊያ ሰዓት ተቃረበ፡፡ በዚህ ሰዓት ግን በመካከል መላአከ ሞት በድንገት ተከስቶ በድግሱ አጠገብ ሲያልፍ፣ የንጉሡን አጫዋች ትኩር ብሎ አይቶት ይሄዳል፡፡
   ያ የንጉሥ አጫዋች ክፉኛ ልቡ ደነገጠ፡፡ ንጉሡና ንግሥቲቱ ወደ መኝታ ቤታቸው ይገባሉ፡፡ ድንክዬው የንጉሡ አጫዋችም ወደ መኝታው ይሄዳል፡፡ ሆኖም እንቅልፍ አልወሰደውም፡፡ ያስጨነቀው ነገር አለ፡፡ ስለዚህ ወደ ንጉሡ መኝታ ቤት ሄዶ በሩን አንኳኳ፡፡
  “ማነህ” አሉ፤ ንጉሡ
  “እኔ ነኝ አጫዋችዎ”
  ተነስተው አገኙት፡፡
  “ምነው ምን ሆነሃል? አሉት”
  “ዛሬ እያጫወትኮት ሳለ መላዕከ ሞት መጥቶ ትክ ብሎ አይቶኝ ሄደ፡፡ የምደበቅበት ቦታ ካላገኘሁኝ ይዞኝ ሊሄድ ነው የመጣው፡፡ ልቤ ክፉኛ ፈርቷል፡፡ ንጉሥ ሆይ፤ ያሽሹኝ እባክዎ!”
  ንጉሡም ጥቂት አሰብ አድርገው፤ “ግዴለም በአሁን ጊዜ ሩቅ አገር ህንድ ነው፤ ነገ ጠዋት ወደዚያ ትሄድና ጥቂት ቀን ቆይተህ ትመለሳለህ፡፡ እኔም በፀሎቴ አምላኬን እማፀንልሃለሁ፡፡ በል አሁን ተረጋግተህ ተኛ፡፡” ብለው ወደ መኝታቸው ገቡ፡፡
  ጠዋት የንጉሡ አጫዋች ተሰነዳድቶ ሲጨርስ መርከቡ መጥቶለት ወደ ህንድ አገር ተጓዘ፡፡
  መድረሱን አረጋገጠ፡፡
  ከዚያን ቀን ጀምሮ ነጋ ጠባ ያጫዋቻቸውን ነገር ለማወቅ ሌት ተቀን ፀሎት ማድረሳቸውን ተያያዙት፡፡
  ከአንድ ሳምንት ምህላ በኋላ መላዕከ ሞት ተገለጠላቸው፡፡
  “ንጉሥ ሆይ፤ ምን እርዳታ አስፈለግዎት?” ሲልም ጠየቃቸው፡፡
  “ምነው? አጫዋቼን፣ መንፈስ መሰብሰቢያዬን፣ የቤተ መንግሥት መዝናኛ ፈጣሪዬን፣ የጭንቅ ጊዜ አንደበቴን ልትወስደው አሰብክ? አላሳዝንህምን?” ሲሉ ጠየቁት፡፡
  መላዕከ ሞትም “ንጉሥ ሆይ፤ እርግጥ ነው መጥቼ አይቼዋለሁ፤ ትኩር ብዬም አስተውዬዋለሁ”
  “ታዲያ ስለምን ይዘኸው ልትሄድ አሰብክ?”
  “እኔ ትኩር ብዬ ያስተዋልኩትኮ በአንድ ምክንያት ብቻ ነው፡፡”
  “መላዕክ ሆይ፤ ያ ምክንያትህ ምን ይሆን?”
   “ንጉሥ ሆይ ትኩር ብዬ ያየሁት፣ እኔ ከአምላክ የታዘዝኩት ከህንድ አገር አምጣው ተብዬ ነው፤ እዚህ እየሩሳሌም ውስጥ ምን ያደርጋል ብዬ ነው!” አለ፡፡
  እንግዲህ የንጉሥ አጫዋች ወደማይቀርለት ቦታ፣ ወደተፃፈለት ሥፍራ ሄዷለ ማለት ነው፡፡
  *   *   *
  ጐበዝ፤ “የተፃፈ ነገር ከመፈፀም አይቀርም” የሚለውን የመጽሐፍ ቃል አለመዘንጋት ነው፡፡
  እንቁ የልጅነት የሥነ ጽሑፍ አባታችን ደራሲ ከበደ ሚካኤል፤
  “እንዲሁም በዓለም ላይ፣
  አለ አንዳንድ ነገር
  በዚህ ቢሉት በዚያ
  ከመሆን የማይቀር!”
  ሲሉ ጠቅለል አድርገው ገልፀውልናል፡፡ ምንም እንኳ ሰዋዊ በሆነው ተጨባጭ አለም የህይወት ነብር - ወገ ቢር ህሊናዊው (Subjective) እንዲሁም ነባራዊው (Objective) ብለን በመክፈል የሁለቱን ውህደት እንደ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተያያዥ መስተጋብር፣ ትርጉም ሰጥተን ለህልውናችን ፍቺ ለማድረግ በመሞከር የእጣ ፈንታን ፍፃሜ - ነገር ለማመላከት የሰው ልጅ ዓለም ከተፈጠረ፣ ታሪክ ከተጀመረ፣ ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ እንደ ጣረ፣ እንደተፍጨረጨረ አለ፣ በመንፈስም በሥጋም ጽድቅና ኩነኔን፤ ክፉና በጐን “በተቃራኒዎች አንድነትና ትግል” መንዝሮ በተለያየ መንገድ ለማጤን ሲሞክር መኖሩ ያለ፣ የነበረና ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡
  ከሰፊው ሁለንተናዊ ዓለም ወደ ጠባቡ ዓለም መምጣት አይቀሬ ነው፡፡ ዛሬ ከዓለም በታሪክ ታይቶና ሆኖ በማያውቅ መልኩ (unprecedented) የተከሰተ፣ ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረ፣ ጠቢባንን ሁሉ የተፈታተነ፣ ቀሳፊ በሽታ (ኮሮና) ሰለባ ከመሆኗ በመነሳት እንደ የኃይማኖቱ ፈርጅ በፀሎትና በምህላ እልባቱን መማፀን ከቤተሰብ ወደ ህብረተሰብ፣ ከሀገር ወደ ዓለም በሰፋ መልኩ ምኞትና ተስፋውን የሙጥኝ ማለቱን ሌት ተቀን ተያይዞታል፡፡ ይህም ግዴታ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ያም ሆኖ በሳይንሳዊ አመክኖዮአዊና ሥነ አዕምሮአዊ መንገድ የህክምና ቴክኖሎጂን እጅህ ከምን እና የየአቅምን ጥንቃቄና የችግር ማቃለያን መንገዶች ሁሉ መሻቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ጥናቱን ይስጠን!
  አገራችንም በሽታው መግባቱ ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ የተያዙ፣ ተገልለው ማቆያ ገብተው ተገቢው ክትትል የሚደረግላቸው፣ ያገገሙና ህይወታቸው ምን ደረጃ እንደደረሰ ያለፈውንና የአሁኑን ስታትስቲካዊ ቀመር ለማስቀመጥና የአቅምን ያህል እለታዊ ጊዜያዊ ዘገባ ማቅረቡ ፍፁም ባይባልም፣ እየተሻሻለና እድገቱ ለውጥ እያሳየ መምጣቱን፣ ቁጥሩ ግን እየበዛ መቀጠሉን የማሳወቅና መረጃ የመስጠት ተግባሩ የሚበረታታ ጉዳይ ነው፡፡ ያም ሆኖ የህዝባችን የአንድ ሰሞን ብቻ ስነስርዓት አክባሪነትና መመሪያ ተቀባይነት የጉዳዩን አሳሳቢነት በአስከፊ መልኩ እንድንታዘብ ያደረገ ሲሆን፤ አሌ የማንለው የችግር አሻራውን ተራራ አከል ደረጃ እየደረሰ መሆኑን ማጤን ተገደናል:: የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ ውትወታዊ ማስጠንቀቂያውንና ትምህርታዊ ምክሩ ቢያታክትም፣ ዛሬም መደገሙ ተገቢ ነው እንላለን፡፡
  በየቦታው የሚፈነዳው ግጭትና ሁከት፣ ነውጥና የመሣሪያ ዝውውር (የዕጽም ጭምር) ጐርፍ፣  በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው፡፡ “የምበላው ሳጣ ልጄ ጥርስ አወጣ” እንደሚባለው ነው፡፡ ዛሬ ትምህርት በተቋረጠበት፣ ሥራ አገም ጠገም በሆነበት፤ ከኮሮና ውጭ ያሉ የሌሎች የበሽታ ሁኔታ አስጊ በሆነበት ሥራ አጥነትና መፍትሔው መላው በጠፋበት ሁሉንም ለማቃለል መሞከሩ ቢበረታታም፤ ችግራችን ዛሬም ጭንቅላት የሚያሲዝ ነው፡፡
  “ግመሎቹ ይሄዳሉ ውሾቹ ይጮሃሉ” የሚለው የሚታይ ቢሆንም፤ ግመሎቹም አልቆሙም ውሾቹም ላንቃቸው አልተዘጋም፡፡ በየትኛውም መስክ ያሉ ተቃዋሚ ድርጅቶችም የመደራደሪያ ጠረጴዛ ከነመኖሩም አለ ብለው ማሰቡን ያጡት ይመስላሉ፡፡
  ድርድርን የበላው ጅብ አልጮህ ማለቱ እርግጥ ነው፡፡ በአንፃሩ በሌላው ወገን ጭራሽ ዘራፌዋውም እንደቀጠለ ነው፡፡ ጐረቤት አገሮች በአባይ ግድብ አይናቸው እንደቀላ መሆኑ፤ አሳሳቢነቱን ጋብ አላደረገውም፡፡ በአንጻሩ ችግኝ መትከሉና ወቅቱን መሻማቱ ብልህነት ነው፡፡ በዚህ መሃል ስርዓተ አልበኝነትን በቅጡ መዋጋት ተገቢ ነው:: “ወንጀሎች ሌብነቶች፣ የችሎት ግቢ መጣበቦች ጥሩ ምልኪ መስለው አይታዩንም፤ ዲሞክራሲው ዛሬም ውጥር ግትር ነው፡፡ የእኩልነት የወንድማማችነት የመብትና ነፃነት ሁኔታ የልባችን ሞልቷል ማለት ገና አያስደፍርም፤ ሥር ነቀልና ጥብቅ ሂደትን ይጠይቃል፡፡ የግድቡ ሙሌት የአንድነት መንፈስ መፍጠሩን ማድነቅ ተገቢ ሆኖ፣ አሁንም ጥንቃቄንና በዓይነ ቁራኛ ማየትን ይሻል፡፡ የላዕላይ - መዋቅሩ የሥልጣን ሽግሽግ ከ1966ቱ “ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም” የሚል መፈክሩ ወጥቶ እውነተኛ የለውጥ መንፈስ ማንገቡን እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ዞሮ ዞሮ የዜሮ ድምር ጨዋታ እንዳልሆነ ያየነውን ያህል፣ የፓርኮች፣ የቅርስ ቦታዎችና ልዩ ልዩ የቱሪስት መስህቦች ህልውና ላይ ትኩረት መስጠቱ ይበል ማሰኘቱን በአጠቃላይ አዎንታዊ ጉዳዮች አንፃር አጥጋቢ መሆኑን ስናይ፤ “ረሀብ ትችላለህን?” ቢሉት” ኧረ ጥጋብም እችላለሁ አለ” የተባለውን ተረት ሳንዘነጋ፤ መሬት በረገጠ መልኩ መጓዝ ይጠበቅብናል፡፡

  Read more
 • የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ለየአገሩ 200 ሺሕ ዶላር ሊሰጥ ነው

  የፊፋ ድጋፍም ይጠበቃል ተብሏል

  ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ዓመታዊ የእግር ኳስ መርሐ ግብሮቻቸውን በዓለም አቀፉ ኮቪድ 19 ወረርሽን ምክንያት በሰረዙበት በዚህ ወቅት፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ለአባል አገሮቹ የገንዘብ ድጎማ ሊያደርግ መሆኑ ታወቀ፡፡ ኮንፌዴሬሽን ለእያንዳንዱ አገር 200 ሺሕ ዶላር ሊሰጥ ማቀዱ ተነግሯል፡፡

  የ54 አገሮች ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችን የሚያስተዳድረው ካፍ፣ በየዓመቱ በመደበኛነት ከሚያከናውናቸው ውድድሮች መካከል የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግና የአፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ይሁንና ሁሉም በወረርሽኙ ምክንያት ውድድሮቹ እንዲሰረዙ አድርጓል፣ የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን በሚመለከት አሁን ላይ ምንም ያለው ነገር የለም፡፡

  የዘንድሮን የውድድር ዕጣ ፈንታ በሚመለከት ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ስለመደረጉ ወይም ስለመሰረዙ ውሳኔ ላይ ባይደርሱም፣ 16 አገሮች መደበኛ ውድድሮቻቸውን መሰረዛቸው ይፋ አድርገዋል፡፡

  ኢትዮጵያ የዓመቱን ውድድር ከመሰረዟም በላይ በሚቀጥለው ዓመት በአፍሪካ የክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግና የክለቦች ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውክልና እንደማይኖራት ለጊዜውም ቢሆን ይፋ አድርጋለች፡፡ የተቀሩት 15 አገሮች ደግሞ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ውድድሩ እስከተቋረጠበት ድረስ በደረጃ ሰንጠረዡ በተቀመጠላቸው ውጤት መሠረት የሚያሳትፏቸውን ክለቦች በማሳወቅ ውድድሮቻቸውን መሰረዛቸው ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ እነዚህም ቡርኪና ፋሶ፣ ጋምቢያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሞሪሸስ፣ አንጎላ፣ ኬቨርዴ፣ ጊኒ፣ ቶጎ፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ካሜሮን፣ ሩዋንዳ፣ ኒጀር፣ ኮንጎ ብራዛቪልና ላይቤሪያ ናቸው፡፡

  አኅጉራዊው ተቋም እንደ አውሮፓና መሰል አኅጉሮች በእሱ ሥር የሚያስተዳድረውን እግር ኳስ ወደ ገንዘብ በመለወጡ ረገድ ክፍተኛ ክፍተት ያለበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁንና ካፍ በየዓመቱ ለአባል አገሮቹ የሚሰጠውን የገንዘብ ድጎማ ሳያቋርጥ ለመስጠት ማረጋገጫ መስጠቱ ታውቋል፡፡ ዘገባዎች የካፍን ድረ ገጽ በመጥቀስ የተቋሙን ውሳኔ ይፋ አድርገዋል፡፡

  በሌላ በኩል የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) እንደ ካፍ ሁሉ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ለመሰሉ በእግር ኳስ ደረጃቸው በዝቅተኛ ደረጃ ለሚጠቀሱ አገሮች የሚሰጠው ዓመታዊ የገንዘብ ድጎማ እየተጠበቀ መሆኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡

  ከፊፋ የሚጠበቀው የገንዘብ መጠን በየዓመቱ በመደበኛነት ከሚሰጠው 500 ሺሕ ዶላር በተጨማሪም ለኮቪድ-19 ወረርሽኝና ለመሳሰሉት አስቸኳይ ለሆኑ ጉዳዮች ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ከዚህ በፊት የተናገሩትን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

  ከዚህ በተጓዳኝ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የአውሮፓ አገሮች የእግር ውድድር ከተቋረጠበት እንደሚቀጥል ተረጋግጧል፡፡ በኢትዮጵያውያን የሚዘወተረውና የተለመደው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሰኔ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚጀመር ሲገለጽ፣ የጀርመን ቡንደስሊጋ ግን ከሁለት ሳምንት በፊት መጀመሩ ይታወሳል፡፡

  Read more
 • ‹‹የዜጎችን ሕይወት ማዳን የመጀመርያውና ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ በመጪው ዓመት ከፍተኛ ገንዘብ በመጠባበቂያነት እንይዛለን›› ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ

  ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በገንዘብ ሚኒስቴር የፊሲካል ፖሊሲና የፋይናንስ ዘርፍ የተመለከቱ ጉዳዮችን በሚኒስትር ዴኤታነት እንዲመሩ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ተሹመው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ከመሆናቸው በፊት የብሔራዊ ፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን፣ የአሁኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በመተካት ነበር የመንግሥት ሹመትን ተቀብለው መሥራት የጀመሩት፡፡ ለአራት ወራት በኮሚሽነርነት የመሩትን ተቋም አስረክበው ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ከመጡ አንድ ዓመት ከስምንት ወራት በላይ ያስቆጠሩት ኢዮብ (ዶ/ር)፣ በግሉ ዘርፍ በርካታ ተሞክሮ ያካበቱና የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክን ሲመሩ የቆዩባቸው ጊዜያት ይታወሳሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሜሪላንድ በፖለቲካል ኢኮኖሚ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን የሠሩት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በዓለም አቀፍ ፖሊሲ በተለይም በዓለም አቀፍ የንግድ ፖሊሲ  ከጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የማስትሬት ዲግሪያቸውን በማግኘት በንድፈ ሐሳብ በተሞክሮም የዳበረ ልምድ አካብተዋል፡፡ በመንግሥት የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ላይ ሰፊ ሚና ያላቸው ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት መላውን ዓለም ባዳረሰው የኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ እየደረሰ ስላለው ጫና፣ እንዲሁም መንግሥት እየወሰዳቸው ስለሚገኙት የፖሊሲ ዕርምጃዎች ኢዮብ (ዶ/ር) ከሪፖርተር ጋር ያደረጉትን ቆይታ ብርሃኑ ፈቃደ አጠናቅሮታል፡፡

  ሪፖርተር፡- በኮሮና ምክንያት ኢትዮጵያ ምን ያህል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎቿን ታጣለች?

  ኢዮብ (ዶ/ር)፡- የኮሮና ወረርሽኝ ለየትኛውም ዓለም ኢትዮጵያን ጨምሮ ከባድ ፈተና ነው፡፡ ምን ያህል ፈተና ሊያመጣብን ይችል ነበር? ምን አጣን? ምንስ ተጎዳን? የሚሉትን ለያይቶ መመልከቱ ጠቃሚ ነው፡፡ በአጠቃላይ ወረርሽኙ በባህሪው የሰዎችን ማኅበራዊ መስተጋብር የሚከለክል ከመሆኑ አኳያ፣ በጤና በኩል ከሚመጣው ጉዳት በማያንስ በኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በሰዎች እንቅስቃሴ ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው ለጉዳት ተጋላጭ ናቸው፡፡ በአገልግሎት መስክ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስን ይጠይቃሉ፡፡ በምርት ሒደትም ሰዎች በጋራ ሆነው ይሠራሉ፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛና አሉታዊ ተፅዕኖ እየደረሰ ነው ያለው፡፡ በመሆኑም ጉዳቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ደጋግመን እንደምንገልጸው ይህንን ጉዳት በመረዳት ገና ከጅምሩ የኮሮና ምላሻችን በጥንቃቄ የተዘጋጀ፣ የዜጎችን ሕይወትና ኑሯቸውን የጠበቀ ምላሽ መስጠት አለብን የሚል አቋም ስለነበረን ብዙ ርቀት ሊያስኬደን የሚችል ስትራቴጂ የዘረጋን ይመስለኛል፡፡ በዚህ መንገድ ምላሽ የምንሰጥበት ስትራቴጂ ባይኖረን ኖሮ ጉዳቱ ከባድና በኢኮኖሚው ላይም ዘለቄታዊ ጉዳት አድርሶ ይሄድ ነበር፡፡ አሁን እንደሚታየው በመጠኑም ቢሆን ደህና በሚባል ሁኔታ እየተቋቋምን ነው፡፡ ምርታማ ዘርፎችን በነበሩበት መንገድ እያመረቱ እንዲቆዩ ማድረግ አማራጭ የለውም፡፡ ግምገማውን ስናየው የምግብ ዕርዳታ የሚፈልግ 15 ሚሊዮን ተጨማሪ ሰው ከተፈጠረ፣ በርካታ ዜጎች ለሥራ አጥነት የሚዳረጉ ከሆነ፣ እነዚህ ችግሮች እንዳይፈጠሩ የምንወስደው ዕርምጃ ችግሮቹ ከመጡ በኋላ ከምንወስደው ዕርምጃ ይልቅ ትልቅ ውጤት ስለሚኖረው በዚያ መንገድ ምላሽ እየሰጠን ነው፡፡

  በሥራ አጥነት ላይ የተሠራው ትንበያ አሳሳቢ ነበር፡፡ ነገር ግን የሰጠነው ምላሽ ተቋማት እንዴት አድርገው ሠራተኞቻቸውን ይዘውን ያቆዩ? ወደሚል የፖሊሲ ምላሽ በመሄድ መንግሥትም ይህንን የሚያግዙ የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ ነው፡፡ ተቋማት እንዳይሞቱና የዜጎች ህልውና፣ ደኅንነታቸውና ኑሯቸው እንዲጠበቅ ምን እናድርግ በሚለው መንገድ የሄድነው፡፡ ተቋማት ሠራተኞቻቸውን እንዳይበትኑ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መከልከል ብቻ ሳይሆን፣ ይኼንን በፖሊሲ እንደግፍ ብለን ለምሳሌ በጣም ከተጎዱት መካከል ዋናው የቱሪዝምና የሆቴል ዘርፍ እንደ መሆኑ መጠን፣ በዘርፉ ያሉትን ተቋማት ሠራተኞቻቸውን ማቆየት እንዲችሉ ምን እናድርግላችሁ ብለን በምክክር ሐሳባቸውን ለመረዳት ሞክረናል፡፡ እነሱም አፋጣኝ የአጭር ጊዜ ብድር ካገኘንና የብድር ዕዳዎቻችን ከተሸጋሸጉልን ችግሩ መቼ እንደሚያበቃ ባይታወቅም ማለፍ እንደሚቻል ሐሳብ ስላቀረቡ በዚሁ መንገድ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ ይህ ችግር ካለፈ በኋላም በቶሎ አገግመን ወደ ሥራ የምንገባው በእጃችን ያለ ሠራተኛ ሲኖር ነው፡፡ ያልበተነው ሠራተኛ ሲኖር፣ ስናሠለጥነው የቆየነው ሠራተኛ ለሥራ ዝግጁ ሆኖ ሲገኝ ወደ ሥራ በቶሎ መግባት ቀላል ይሆናል፡፡

  ሌላው ጉዳይ ግብርናን ጨምሮ አምራቹ ዘርፍ ተጨማሪ ግብዓት እያመጣ ነው ወይ? ገበሬውስ አስፈላጊውን ርቀት ጠብቆ በሥራው ላይ ነው ወይ? የሚሉትን ስናይ አዎን የምርት ሥራ እንዳይቋረጥ አድርገናል፡፡ ገበሬው የምርት ግብዓቶች በቶሎ እንዲያገኝ፣ ከዚህም አልፈን የምግብ ዕጦት ሥጋት ሊኖር ስለሚችልና የዓለም የአቅርቦት ሰንሰለትም ችግር ውስጥ መውደቁ ስለሚያሠጋ፣ በአገራችን ያለውን ምርት ማሳደግ አለብን በማለት የተለዩና ከዚህ ቀደም ያልነበሩ አዳዲስ አሠራሮችን ተከትለናል፡፡ ለምሳሌ ለገበሬው የውኃ መሳቢያ ፓምፕ ማሠራጨት በዕቅድ ያልነበረ ነው፡፡ ወደ ሥራ ያልገቡ መስኖዎችን በቶሎ አጠናቆ ወደ ሥራ ማስገበት ሌላኛው ዕርምጃ ነው፡፡ የማንም መሬት ፆም እንዳያድር፣ በስኳር ኮርፖሬሽንና በክልሎች መካከል  የባለቤትነት ጥያቄዎች ያሉባቸው፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በዕዳ የያዛቸውና ሌሎችም ባሉበት ሆነው ፆም ሳያድሩ ምርት እንዲመረትባቸው፣ ያሉትን ችግሮች ግን ዋል አደር ብለን እንነጋገርባቸዋለን በማለት ወሳኝ የፖሊሲ ዕርምጃ ወስደናል፡፡

  ጉዳቱ ከመጣ በኋላ ለመቋቋም ከምናደርገው መረባረብ ይልቅ፣ ሳይመጣ ቀድመን ምላሽ መስጠት የምንችልበትን አቅም መገንባት ላይ ያተኮርነው፡፡ በአጠቃላይ በኢኮኖሚው ላይ ጉዳት አለ፡፡ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) እስከ ሦስት በመቶ ቅናሽ እንደሚኖር ግምት ወስደናል፡፡ ደግነቱ ግን የእኛ በጀት ዓመት ከውጮቹ የተለየ በመሆኑ፣ የበጀት ዓመቱን የዘጠኝ ወራት ገደማ ሥራ በጨረስንበት ወቅት ነው ወረርሽኙ የመጣው፡፡ ከዚያ በፊት በነበሩት ጊዜያት የመንግሥት ገቢ መቶ በመቶ በሚባል ውጤት ደረጃ ስንሰበስብ ቆይተናል፡፡ ጉዳቱ የመጣው በተቀሩት ወራት ወቅት እንደ መሆኑ፣ የጉዳቱ መጠንም በመጨረሻው ሩብ ዓመት ላይ በሚደርሰው መጠን የሚለካ ይሆናል፡፡ በዓለም ላይ ያደረሰው ጫናም ተደምሮ የሦስት በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ጉዳት ማድረሱ በጣም ትልቅ ተፅዕኖ ነው፡፡ እስካሁን የማገገሚያ ዕቅዱ ከአደጋ ጊዜ ምላሽ አሰጣጥ ዕቅድ ጋር ተዛምዶ እንዲሄድ መደረጉ በብዙ የረዳን ይመስለኛል፡፡ ጥሩ ውጤት ያስገኘ ስትራቴጂ እንደተከተልን አስባለሁ፡፡       

  ሪፖርተር፡- እስከ ሦስት በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ቅናሽ እንዲመዘገብ የኮሮና ወረርሽኝ ስለሚያስገድድ በንግድ ሚዛንና በክፍያ ሚዛን ጉድለት ላይ፣ በውጭ ሐዋላ ገቢና በሌሎችም መስኮች ላይ የሠራችኋቸው ትንበያዎች አሉ?

  ኢዮብ (ዶ/ር)፡- ችግር የሆነብን ትንበያው በየቀኑ ተለዋዋጭ እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡ መጀመርያ ላይ ለልማት አጋሮች ድጋፍ በሚል በሠራነው ሥራ ላይ ያስቀመጥናቸው ትንበያዎች የውጭ ሐዋላ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጎዳ፣ በኢንቨስትመንት ፍሰትም ላይ እስከ 40 በመቶ ቅናሽ ሊመዘገብ እንደሚችል፣ በወጪ ንግድ ላይ ያስቀመጥናቸው ትንበያዎች አሉ፡፡ በሌላ በኩል በመከላከል ሥራ ላይ የተከተልነው ስትራቴጂ ያመጣቸው ውጤቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ በቡና ወጪ ንግድ ላይ ከጠበቅነው በላይ ማንሰራራት ተመልክተናል፡፡ አንዳንድ አገሮች ከገመትነው ጊዜ ቀድመው ድንበሮቻቸውን በመክፈታቸው የአበባ የወጪ ንግድም በመጠኑ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ በመሆኑም ቀድመን ያወጣናቸውን ትንበያዎች እንደገና መከለስ ሊኖርብን ነው፡፡ አጠቃላይ ጉዳቱ ምን ያህል እንደሚሆን ለማወቅ በጀት ዓመቱ ካለቀ በኋላም ቢሆን ተመራጭ ነው፡፡ በየሳምንቱ እየተቀያየረ ባለው የትንበያ ሁኔታ ላይ ጊዜ ማጥፋት ብዙም ጠቀሜታ አይኖረውም፡፡ ይሁን እንጂ የሐዋላ ገቢና የኢንቨስትመንት ፍሰት በመቀነሱ፣ ወይም ገንዘባቸውን እዚህ ለማምጣት ወስነው የነበሩ ኩባንያዎች በተለያዩ ችግሮች ተይዘው ይገኛሉ፡፡ ኢንቨስትመንት የሚለካው ውሳኔ ለተሰጠበት የሥራ መስክ የሚያስፈልገው ገንዘብ እዚህ መጥቶ ሲመዘገብ ነው፡፡ እነዚህ መቀነሳቸው አልቀረም፡፡ በሌላ በኩል ከነዳጅ የምናገኘው የዋጋ ዕፎይታ ይኖራል፡፡ በገቢ ንግድ ረገድ ወሳኝ በሚባሉት ላይ ለምሳሌ የሕክምና አቅርቦቶች በምንም መንገድ አይቀንሱም፡፡ ማዳበሪያና ምግብ ነክ ሸቀጦች ቅድሚያ አግኝተው እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ በግሉ ዘርፍ አማካይነት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሸቀጦች መቀነሳቸው አይቀርም፡፡ በተለይም ቅድሚያ የማይሰጣቸው ሸቀጦች ብዙም ትኩረት ላያገኙ ይችላሉ፡፡ በጠቅላላው ግን አሁን ትንበያዎችን መሥራት ትተናል፡፡ ቀድሞ በተሠራው ላይ ሊኖሩ የሚችሉ ለውጦችን እያየንና እያስተካከልን፣ በዓመቱ መጨረሻ ላይ የደረሰውን ጉዳት አጣምረን ሪፖርት እናደርጋለን፡፡

  ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ሁኔታ የኮሮና ወረርሽኝ በከፍተኛ መጠን ይስፋፋል ተብሎ የተተነበየው ከሰኔ ወር በኋላ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የተለየና ለአደጋ ጊዜ ተብሎ የተዘጋጀ የመጠባበቂያ በጀት አለ?

  ኢዮብ (ዶ/ር)፡- አዎን፡፡ በዚህ ዓመት እንኳ ካየን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያፀደቀው የበጀት ማስተካከያ አለ፡፡ ይኼ በሰፊው ለምን አስፈለገ ከተባለ ወጪያችን በከፍተኛ መጠን ጨምሮ ገቢያችን እየቀነሰ በመምጣቱ ነው፡፡ ወጪያችን እንዴት ጨመረ ካልከኝ፣ በሽታውን ለመከላከል የምናወጣቸው ትልልቅ ወጪዎች ስላሉ ነው፡፡ ለጤና መስክ ብቻ በጤና ሚኒስቴር የተጠየቀው በየጊዜው የሚወሰድ 15 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል፡፡ ለአደጋ መከላከል ሥራው በተለይም በቂ ምግብ ለማቅረብ የሚወጣ ወጪ አለ፡፡ በቅርቡ 600 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለመግዛት ጨረታ መውጣቱ ይታወቃል፡፡ ተቋማትን ለመደገፍ ለምሳሌ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች፣ ለኅብረት ሥራ ማኅበራትና ለአነስተኛ ገንዘብ አቅራቢ ድርጅቶች በልማት ባንክ በኩል 4.5 ቢሊዮን ብር ድጋፍ እንዲያገኙ ተወስኗል፡፡ ይህ ሁሉ ያልታሰበ ተጨማሪ ወጪ ነው፡፡ እነዚህን በገንዘብ ለመደገፍ የፊስካል በጀት ማስተካከያ ማድረግ አስፈልጎናል፡፡ በገቢ ደረጃ የጠበቅነው አልተገኘም፡፡ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ያገኘነው ድጋፍ ቢኖርም ለተጨማሪ ብድር መሄዳችን አይቀርም፡፡ ተጨማሪ የበጀት ማስተካከያ እንዲፀድቅ ከመጠየቃችን በተጨማሪ የመጪው በጀት ዓመትም ትኩረት ይሰጠዋል፡፡

  በነገራችን ላይ ሁሉም ሰው እየገመተ እንጂ፣ የበሽታው ሥርጭት የሚባባሰው በትክክል ሰኔ ላይ ወይም ሐምሌ ላይ የመሆኑ ነገር በትክክል አይታወቅም፡፡ በታቸለ መጠን መንግሥት በዕውቀት ላይ በተመሠረተ ዕቅድ መመራት ስላላበት፣ በዓለም ላይ ያሉ ምሁራንን ከኢትዮጵያውያን ጋር አካተን፣ የሳይንሳዊ አማካሪ ቡድኑን ጨምረን የበሽታው ጉዳት እየበሳ የሚመጣው መቼ እንደሚሆን ለመተንበይ ተሞክሯል፡፡ አሳሳቢው ጊዜ ገና ከፊታችን እንደሚመጣ ሥጋቱ አለን፡፡ ሥጋቱን ዝቅ አድርጎ መመልከት አይቻልም፡፡ ጉዳቱ መቼ ነው የሚከሰተው የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ አሳሳቢ ጊዜ እንደሚጠብቀን ግልጽ ነው፡፡ እንደ ንሥር ዓይናችንን በሽታውን ከመከላከሉ ሥራ ላይ ሳንነቅል፣ የተጠናከረ ዝግጅት ማድረግ እንዳለብን የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ አኳያም የመጪው በጀት ዓመት ይህንን ከግምት የከተተ ዝግጅት የተደረገበትና ከእስካሁኑ ጥብቅ የወጪ ፖሊሲ አኳያ እንዲላላ የሚደረግበት የአደጋ ጊዜ ምላሽ መስጫ ዕቅድ ይኖረናል፡፡ የዜጎችን ሕይወት ማዳን የመጀመርያውና ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ፣ በመጪው ዓመት ከፍተኛ ገንዘብ በመጠባበቂያነት እንይዛለን፡፡ በጀቱም ከተመለደው አካሄድ ከ60 እስከ 70 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ኖሮት ይዘጋጃል፡፡ የሪፎርም ሥራችን በዚህ ጊዜም ስለማይቆም የገቢ መሰብሰብ አቅማችንን በማሻሻል እንሠራለን፡፡ የበጀት ጉድለቱ ቢሰፋም ባይሰፋም፣ ሰፊ የፊስካል በጀት ይኖራል፡፡

  ሪፖርተር፡- ለተጨማሪ በጀት የጠየቃችሁት የገንዘብ መጠን ምን ያህል ነው?

  ኢዮብ (ዶ/ር)፡- ለፓርላማው ቀርቦ እንሚፀድቅ የሚጠበቀው ተጨማሪ በጀት 48.5 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህን ገንዘብ የጠየቅነው የታየውን የገቢ ቅናሽ ለማካካስ ጭምር ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- መንግሥት በታክስ ምሕረትና ዕፎይታ እስከ 78 ቢሊዮን ብር ገቢ ሊያጣ የሚችልበት አጋጣሚ እንደሚኖር አስታውቀው ነበር፡፡ በታክስ ምሕረቱ ላይ በተለይ እስከ 2007 ዓ.ም. የተከማቸው የአሥር ዓመታት የታክስ ዕዳ በመንግሥት ድክመት ጭምር ካለመሰብሰቡ አኳያ፣ እንድ ድጋፍ ሊቆጠር አይገባም የሚሉ አጨቃጫቂ ጉዳዮች ሲነሱ ሰምተናል፡፡ ይህንን እንዴት ነው ያያችሁት?

  ኢዮብ (ዶ/ር)፡- በደንብ በዝርዝር ነው ያየነው፡፡ ከጠቅስከው ውስጥ እስከ 68 ቢሊዮኑን ብር በተሰብሳቢ ሒሳብ ውስጥ የነበረ ገንዘብ ነው፡፡ አንዳንዱ እንደጠቀስከው ለዓመታት ሳይሰበሰብ የቆየ ነው፡፡ በክርክር ሒደት ላይ ያሉና ትኩስ፣ በኦዲት የወጡ አዳዲስ ሒሳቦችም አሉ፡፡ ደረጃቸው ይለያያል፡፡ ማየት ያለብህ ነገር የተሰብሳቢ ሒሳቦች ተፅዕኖ ነው፡፡ ተቋማት በዚህ ዕዳ የተነሳ ወይ ንብረታቸው ተይዞባቸዋል ወይም የባንክ ሒሳባቸው ተዘግቶባቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ማከናወን ተስኗቸዋል፡፡ የእኛ የአደጋ ጊዜ ምላሽ የዜጎችን ሕይወትና ኑሯቸውን መጠበቅ ነው ካልን፣ እንዲሁም አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ተጋላጭ ሳይሆን እንደነበረ እንዲቆይ ማድረግ ከመሆኑ አኳያ፣ በታክስ ክርክር ምክንያት ዕግድ ውስጥ የሚገኝ፣ ንብረቱ የተያዘበት፣ የባንክ ሒሳቡ የተዘጋበትን ተቋም ከዚህ ክርክር አውጥተህ ወደ ሥራ እንዲመለስ አደረግኸው ማለት ሰዎች ዳግም ሥራ እንዲያገኙ፣ ተጨማሪ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖር ዕድል ፈጠርክ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በጣም ትርጉም ያለው ድጋፍ ነው፡፡ ድጋፍ አይደለም ለሚሉ ሰዎች ድጋፉን ያገኙትን ሰዎች ሄዶ መጠየቅ ነው ያለባቸው፡፡ እነሱ ናቸው ምን ያህል ትልቅ ዕፎይታ እንዳስገኘላቸው ሊገልጹ የሚችሉት፡፡ የእኛ ግምገማ ግን ለግሉ ዘርፍ ትልቅ ዕፎይታ የሰጠ ዕርምጃ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ የመንግሥትን ገቢ ያሳጣል ወይ ከተባለ ያለ ምንም ጥርጥር አዎ፡፡ ነገር ግን ዛሬ የምናጣው ገቢ ሳይሆን እነዚህ ተቋማት አገግመውና ወደ ሥራ ገብተው፣ በመጪው ዓመትና ከዚያ በኋላ የምናገኘው የታክስ ገቢ ብሎም ሰዎች ሥራ አግኝተው መኖራቸው የሚያስገኘው አገራዊ ጥቅም ይበልጣል በማለት ነው ድጋፉን የሰጠነው፡፡ ትልቅ ትርጉም ያለው ድጋፍ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- የቱሪዝምና የሆቴል ዘርፍ ያገኘውን ድጋፍ ጠቁመው ነበር፡፡ ጥያቄያችን በከፊል ምላሽ አግኝቷል እያሉ ነው፡፡ የብድር ክፍያ ወደ አንድ ዓመት ይራዘምልን የሚለው ጥያቄያቸው የመንግሥትን ምላሽ እየጠበቀ እንደሚገኝ በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ ማኅበራት እየተናገሩ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ የሰጣችሁት ምላሽ ምንድነው?

  ኢዮብ (ዶ/ር)፡- ይህንን ጥያቄ በዝርዝር ነው ያየነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም ከዘርፉ አመራሮች ጋር ውይይት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ መጀመርያ አካባቢ የነበረው ዕሳቤ ባንኮች የነበረባቸው የገንዘብ ችግር ከተፈታ፣ የተቋማቱን ብድር የማራዘም ወይም ተጨማሪ ብድር የመስጠት ሥራ ይሠራሉ የሚል ነበር፡፡ አንዳንድ ባንኮች ሙሉ በሙሉ ለዚህ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በተለይ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ያሉት ጥያቄያችን አልተመለሰም፣ ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልገናል የሚል ጥያቄ በማቅረባቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ አመራሮች ይህንን ጥያቄ ዳግመኛ ተመልከተው፣ እነዚህ ተቋማት አስቸኳይ የአጭር ጊዜ ብድር እንዲያገኙ ተመቻችቶላቸዋል፡፡ ብድሩንም እየወሰዱ ነው፡፡ ጥያቄያቸው በተለየ መንገድ ነው ምላሽ ያገኘው፡፡ የባንኮች ፕሬዚዳንቶችንና የባንኮች ቦርድ ኃላፊዎችን ባካተተ ውይይት፣ ብሔራዊ ባንክ ከሚያስተላልፋቸው ትዕዛዞች ይልቅ ከባንኮች የሚመጣው መፍትሔ ይሻላል የሚል አሳታፊ መፍትሔ በመከተል፣ ከባንኮች በመጣ የመፍትሔ ሐሳብ መነሻነትም ጭምር ነው ምላሽ የተሰጠው፡፡ በበሽታው ተፅዕኖ እስከ ስድስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ሊፈታ የሚችል ድጋፍ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የቱሪዝም ዘርፉ ካልተነቃቃ አብረን የምናየው ነው፡፡ ነገር ግን የምንሰጠው የኢኮኖሚ ድጋፍ ከጉዳቱ ጋር ተመጣጣኝ መሆን አለበት የሚል ጠንካራ አቋም አለን፡፡ ለስድስት ወራት ከሆነ ሥራ የሚቆመው ለዚህ ጊዜ የሚሆን ብድር ይቀርብና ሥራ ሲጀመር ብድሩም መከፈል ይጀምራል ማለት ነው፡፡ ባንኩም ቢሆን ተጨማሪ ብድር መስጠት የሚችለው ገንዘቡ ሲመለስለት ነው፡፡ በጠቅላላው ግን የቱሪዝም ዘርፉ ጥያቄ ተመልሷል ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡

  ሪፖርተር፡- የአገሪቱ ኢኮኖሚስቶች፣ የእናንተ መሥሪያ ቤት፣ እንዲሁም የዓለም ገንዘብ ድርጅት ልዩ ልዩ የሥጋት ትንበያዎችን ሲያወጡ ከርመዋል፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ የብድር መሸከምና መክፈል አቅምን የሚለኩ ተቋማት ከዚህ ቀደም የነበረውን የአገሪቱን ደረጃ ዝቅ አድርገዋል፡፡ አንዱ መነሻቸው አገሪቱ ያለባትን የገንዘብ ችግር፣ እንዲሁም ዕዳ ለመክፈል እንደሚያዳግታት የሚያሳዩ መረጃዎች ናቸው፡፡ የተቋማቱን ሪፖርቶች ተመልክታችኋል?

  ኢዮብ (ዶ/ር)፡- ዓይተናቸዋል ግን ብዙም አላሳሰቡንም፡፡ ኢትዮጵያን ብቻም ሳይሆን፣ በአጠቃላይ አገሮች ናቸው የታዩት፡፡ ደረጃችን ዝቅ ሊደረግ የቻለው በምን መነሻ ነው የሚለውን ማየት ነው፡፡ እነዚህ አገሮች ያለባቸውን ብድር መክፈል አይችሉ ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት አጠቃላይ የብድር አቅም መመዘኛ አመላካቾች ወደ ኔጋቲቭ ዝቅ የተደረጉበት ዋናው ማጠንጠኛ ምክንያት፣ የብድር ዕዳቸውን አይከፍሉ ይሆናል የሚል ነው፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት መንግሥታት ያነሱት ጥያቄ አለ፡፡ በወረርሽኙ ሥጋት ምክንያት ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይሻለናል፣ የዜጎችን ሕይወት የማዳን ተግባር ቅድሚያ ማግኘት አለበት፣ የብድር ክፍያ ይራዘም የሚል ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ በዚህ ምክያት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የአፍሪካ ድምፅ ሆኖ በቀረበው ጥያቄ መሠረት፣ የቡድን 20 አባል አገሮች ለዘጠኝ ወራት ብድር ሳይከፈል እንዲቆይ የሚያስችል ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ ይህ ጥሪ በቂ ግን አይደለም የሚል ክርክር እያነሳን ነው፡፡ በመሆኑም ተቋማቱ ያወጡት የክሬዲት ምዘና በአብዛኛው የተገኘው አገሮች ያለባቸውን ብድር ላይከፍሉ ይችላሉ ከሚል ሥጋት ነው፡፡ ይህንን ያዩ አገሮች ለምሳሌ እነ ኬንያ ከገበያ ላይ ብድር ስለሚያገኙ ሊመጣባቸው የሚችለውን ሥጋት በመገንዘብ፣ አንከፍልም አላልንም በማለት መግለጫ አውጥተዋል፡፡ እኛ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው አንድ ዩሮ ቦንድ ነው ከብድር ገበያ ያገኘነው፡፡ የሬቲንግ ኤጀንሲዎቹ ሥጋት ብድር ላይከፈል ይችላል የሚል በመሆኑ እኛን ብዙም አላሳሰበንም፡፡ የበሽታው ጫና መስመር ሲይዝና ነገሮች ሲስተካከሉ፣ ያወጡትን ደረጃ መልሰው እንደሚያሻሽሉት የሚጠበቅ በመሆኑ ብዙም አላሳሰበንም፡፡ ከእነሱም ጋር ተነጋግረንበታል፡፡

  ሪፖርተር፡- ከሰሞኑ መነጋገሪያ ከነበሩት አንዱ የዓለም ገንዘብ ድርጅት እንደ ወትሮው ሁሉ፣ በዚህ ወቅት የወለድ ምጣኔ የሚመራበት አግባብ ቁጥጥር ከሚደረግበት አሠራር ወጥቶ በገበያ እንዲመራ ይደረግ የሚለውን ጨምሮ፣ አሁንም የምንዛሪ ተመን ላይ ማሻሻያ ወይም ቅናሽ ይደረግ የሚል ጥያቄ ማቅረቡ ነው፡፡ ከተቋሙ ጋር ስለነዚህ ጉዳዮች ተነጋግራችኋል?

  ኢዮብ (ዶ/ር)፡- እነዚህ ጉዳዮች ብዙ ጊዜ ይነሳሉ፡፡ አዲስ አይደሉም፡፡ ትልቁ ነገር እኛ እንደ መንግሥት የያዝነው የሪፎርም አቅጣጫ አለ፡፡ በሦስት ዓመታት ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚውን መዛባቶች አጥርተን እንጨርሳለን ብለናል፡፡ ሪፎርማችን ግን ቁንጽልና በፋይናንስ ዘርፉ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አይሆንም፡፡ የአምራች ዘርፉን እናነቃቃለን፣ የኢኖሚውን መዋቅራዊ ችግሮች እንፈታለን ብለን የያዝነው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አለን፡፡ በዚያ ማዕቀፍ ነው ሁሉንም ነገር የምናየው፡፡ ሐሳቦች ሲነሱ እንሰማለን፡፡ የጠቀመንን እንወስዳለን፣ የማይጠቅመንን እንተዋለን፡፡ ይህ ነው አካሄዳችን፡፡ የተናበበ የማክሮ፣ የዘርፍና የመዋቅር ለውጥ ግን ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ የሚወሰዱት ኢኮኖሚያዊ ዕርምጃዎችም መሠረታዊ የኢኮኖሚ መርሆዎችን የሚከተሉ መሆን አለባቸው፡፡ ከዚህ በፊት እንዳደረግናቸው ዓይነት በግማሽ የበሰሉ በግማሹ ጥሬ የሆኑ መፍትሔዎችን አንተገብርም፡፡ ለምሳሌ የ15 በመቶ የምንዛሪ ለውጥ አድርጋለሁ ስትል፣ ለዚህ ተመጣጣኝ የሆነ ሥራ በአምራች ዘርፉ ላይ ካልሠራህ የወጪ ንግድ ዘርፉ ምላሽ አይሰጥህም፡፡ ስለዚህ እንደ መንግሥት እንዲህ ያለ ያልተናበበ የፖሊሲ ዕርምጃ አንወስድም፡፡ እዚህ ላይ ጠንካራ አቋም አለን፡፡ ማንኛውም ሰው የመሰለውን ሐሳብ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ የሚጠቅመውን መውሰድ፣ የማይጠቅመውን ለምን እንደማይጠቅም ማስረዳትና መተው ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- በዓለም ከኮሮና ማገገሚያና ድጋፍ ዕርምጃዎች ወደ ኮሮና ተፅዕኖ መውጫዎች ያተኮሩ መፍትሔዎች ላይ ትኩረት እየተደረገ ነው፡፡ በኢትዮጵያስ ምን እየተደረገ ነው? ከቀውሱ የሚወጣበት ስትራቴጂስ ምንድነው? 

  ኢዮብ (ዶ/ር)፡- ስትራቴጂ አለን፡፡ ነገር ግን የቀውስ ጊዜ ለብቻው የማገገሚያ ጊዜና ቆይቶ ለብቻ የሚመጣ ስትራቴጂም አንከተልም፡፡ ደጋግመን አብሮ መሄድ አለበት፣ መናበብ አለበት የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ቀውሱ ካለፈ ከስድስት ወራት በኋላ እንደ አዲስ የምናስብበት የኢኮኖሚ ማገገሚያና ከቀውስ መሻገሪያ ዕቅድ ሳይሆን፣ አንዱ ከሌላው አብሮ የሚሄድ ስትራቴጂ ነው የምንከተለው፡፡ የዜጎችን ደኅንነትና ኑሯቸውን የመጠበቅ ሥራ ተቋማት እንዳይሞቱ አብሮ ከመጠበቅ ጋር አብሮ እየተሠራበት ያለ ነው፡፡ ጥያቄው መቼ ነው ይህ ቀውስ አልፎ ስለሌሎች ጉዳዮች የምንነጋገረው ከሆነ፣ እውነት ለመናገር ቀውሱ መቼ እንደሚያበቃ አናውቀውም፡፡ በእርግጠኝነት የምናውቀው ነገር ቢኖር የምንከተለው ስትራቴጂ እየሠራ መሆኑን ነው፡፡ ለጤና አጠባበቅ የሚመከሩና የሚተገበሩ ሥርዓቶችን እያስጠበቅን፣ ቁልፍ የኢኮኖሚ ክፍሎች በበሽታው ሳቢያ እንዳይስተጓጎሉ እያደረግን ነው፡፡ በእኛ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ሥራ በማስቆምና እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ እንዲገታ የማድረግ ዕርምጃ አንከተልም፡፡ አሁንም በዚሁ መንገድ እንቀጥላለን፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ቦታዎች ከፍተኛ የበሽታው ተዛምቶ ከታየ እነሱን ለይቶ በመዝጋት የሚከናወን ሥራ ይኖራል፡፡ በአዲስ አበባ በየትኞቹ ቦታዎች ከፍተኛ መስፋፋት ሊታይ እንደሚችል የሚያሳይ ጥናት ተካሂዷል፡፡ ቢሳካልን ኖሮ ሰው የፈራውን ያህል ፈርቶ፣ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረገና መመርያዎችን እያከበረ በተገቢው መንገድ ራሱን ጠብቆ ሥራውን እየሠራ ቢገባ፣ በሽታውን ከዚህም በላይ ልንከላከለው እንችል ነበር፡፡ በየመንደሩ ስንወርድ የግንዛቤውና የጥንቃቄ ትግበራው ላይ ብዙ ጥረትም ተደርጎ ችግሮች አሉ፡፡ በሽታው እየባሰ በመምጣቱ ግን አሁን ወደ ሕግ ማስከበር ዕርምጃዎች እየተገባ ነው፡፡ መቼ ነው ወረርሽኙ አልፏል ብለን የምናውጀው ከተባለ አናውቅም፡፡ ያንን ያወቅን ዕለት ዜናውን ከሰማን ቀድመን እናበስራችኋለን፡፡

  ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ሁኔታ እስከ ክረምት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው ትልቁ ፍራቻ ያለው፡፡ ከክረምቱ መግባት በፊት የሚጠበቅ ነገር አለ?

  ኢዮብ (ዶ/ር)፡- በፍላጎት ደረጃ እንዳልኩህ ዛሬውኑ ቢያበቃልን ደስ ባለን፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን፣ የዓለም ጉዳይ ነው፡፡ ክትባት ተገኘለት ወይ ሲባል ጅምሮች መታየታቸው ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ የወረርሽኙ ሥርጭት አንድ ቦታ ላይ ደርሶ ሥጋት ወደማይሆንበት ደረጃ ቢደርስ፣ ሁሉም ዓለም የሚፈልገው ነገር ነው፡፡ በእኛ ሁኔታ በርካታ ትንበያዎች አሉ፡፡ አንዳንዶች ኅዳር ላይ ነው ወረርሽኙ ጫፍ ደርሶ የሚመለሰው የሚሉ ይኖራሉ፡፡ በአብዛኛው ምክንያታዊ የሆነው ዳሰሳ በክረምቱ እየተባባሰ ሊመጣ ይችላል የሚለው ነው፡፡ ይህም ቢሆን ግን መላምት ነው፡፡ በጣም አጽንኦት ልሰጥበት የምፈልገው ጉዳይ፣ እነዚህ ሁሉ የጠቀስናቸው ነገሮች መላምቶች ናቸው፡፡ በእርግጠኝነት በዚህ ጊዜ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በዚህ ጊዜ ይወርዳል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር የሚችል የለም፡፡ መጀመርያ ሰሞን የምንሠራው የበሽታው ሥርጭት ማሳያ ሰንጠረዥ በጣሊያን የታየውን ዓይነት የሚመስል ነበር፡፡ ሁሉም የጤና ባለሙያ የበሽታውን ሥርጭት የሚያሳይ ሰንጠረዥና ምሥል እየሠራ፣ በሦስት ሳምንት ውስጥ እዚህ ደረጃ ሊደርስ ይቻላል የሚል ግምት ሲያስቀምጥ ነበር፡፡ ወረርሽኙ በአፍሪካ ደረጃ የራሱን ባህሪ አሳይቷል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በአፍሪካ ያለውን ሁኔታ ዓይቶ አዲስ ትንበያ አውጥቷል፡፡ በፍላጎት ደረጃ ወዲያውኑ እንዲቆምልን እንፈልጋለን፡፡ ምክንያቱም የጀመርናቸው በርካታ የሪፎርም ሥራዎች አሉን፡፡ ከፊታችን ምርጫ ይጠብቀናል፡፡ ሐሳቦች ተጋፍተው ሕዝብ የሚመስለውን የሚመርጥበት ነገር ለመሥራት ጠንካራ ዝግጅት ነበር፡፡ እንደ ኢኮኖሚ ቡድኑ አባል በምርጫ ክርክር ውስጥ ለሕዝቡ ያለንን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የበላይነት አማራጭ ሐሳቦች ለማሳየትና በሕዝቡ ልብ ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ ትልቅ ፍላጎት ነበረን፡፡ እነዚህ ነገሮች ሲዘገዩብህ ያሳስብሃል፡፡ ግን ምን ማድረግ ትችላለህ? ባለበት ሁኔታ መሄድ ነው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ የሚያበቃበትን ቁርጥ ቀን እናውቃለን የሚሉትን አንስማቸው፡፡ ማንም ይህን አያውቅም፡፡

  ሪፖርተር፡- ወደ ፖሊሲ ምላሾቻችሁ እንምጣ፡፡ ከቀረጥ ነፃ ሆነው እንዲገቡ የተፈቀዱ የምግብ ሸቀጦች አሉ፡፡ ፓስታ፣ ማካሮኒና ዱቄትን ጨምሮ ይህንን ዕድል እንዲያገኙ መደረጋቸው፣ በአገር ውስጥ የሚገኙ አምራቾች ላይ ከፍተኛ ሥጋትና ጫና ማሳደሩን የሚያሳስብ እሮሮ እናንተ ጋር ሳይመጣ አልቀረም፡፡ በአገር ውስጥ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ቫትን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ታክስ እየከፈሉ ባሉበት ወቅት፣ ከውጭ በነፃ እንዲገባ መፈቀዱ ትክክል አይደለም እያሉ ነው፡፡

  ኢዮብ (ዶ/ር)፡- ለየትኛውም አስመጪ ይህንን አልፈቀድንም፡፡ ተናበን እየሠራን ነው፡፡ ማካሮኒና ፓስታ ከቀረጥ ነፃ ይግባ የሚል ነገር የለም፡፡ ፍራንኮ ቫሉታ ከሆነ እሱ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ በራሳቸው የውጭ ምንዛሪ ምርት እንዲያስገቡ የፈቀድነበት መንገድ አለ፡፡ በተለመደው የአገራችን የንግድ ሕግ የውጭ ኩባንያዎች በንግድ ውስጥ መሳተፍ አይችሉም፡፡ በተለየ ሁኔታ ግን የኢንቨስትመንት ቦርድ በፈቀደውና የገንዘብ ሚኒስቴርም በሰጠው መመርያ መሠረት፣ በፍራንኮ ቫሉታ እንዲገባ ፈቅደናል፡፡ ነገር ግን የታክስ ሥርዓቱ እንዳይዛነፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል፡፡ ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ የሚፈቀድላቸው አሉ፡፡ ለምሳሌ ስኳር የሚገባው በስኳር ኮርፖሬሽን አማካይነት ነው፡፡ የተወሰኑ የዘይት ምርቶች በድጎማ ለደሃው የኅብረተሰብ ክፍል የሚገዙ አሉ፡፡ ከዚህ ውጭ አቅርቦት እንዲጨምር ፈቀድን እንጂ የተለየ ድጋፍ አልሰጠንም፡፡ ድጋፍም አላደረግንም፡፡ ትኩረታችን የአገር ውስጥ ምርት ላይ ነው፡፡ እናንተም ሄዳችሁ ማየት እንደምትችሉት እያንዳንዱ ኩባንያ በዘርፍ ደረጃ ድጋፍ እየተደረገለትና የገቢ ንግዱ ብዙም እንዳይበረታታ እያደረግን ነው፡፡ ለምሳሌ የፕላስቲክ ፓይፕና መሰል ምርቶችን ለሚያመርቱ ተቋማት የጥሬ ምርት ግብዓት እንዲያገኙ በማስቻል፣ ከውጭ የሚመጣ ምርት እንዳይገባ የመደገፍ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ከዚህ ቀደም የምንሰጣቸው የቀረጥ ነፃና መሰል ማበረታቻዎች የተናበቡ አልነበሩም፡፡ በአንድ በኩል የገቢ ንግዱን እያበረታታ በሌላ በኩል የአገር ውስጥ አምራቹን እየጎዳው መደገፍ የማያስኬድ በመሆኑ፣ አምራቹ የተሻለ የታክስ ማበረታቻ እንዲያገኝና ያለቁ ምርቶች ሲገቡ ተጨማሪ ታክስ እንዲጣልባቸው በማድረግ የተናበበ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡

  Read more
 • ከጥሬ ገንዘብ ዝውውር በላይ ተጨማሪ ገደቦችን እንደሚያስከትል የሚጠበቀው አዲሱ ሕግ

  የኮሮና ወረርሽኝ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ በተለያየ መንገድ እየተገለጸና እየተተነተነ ይገኛል፡፡ በከፍተኛ ደረጃ መዛመት የጀመረው ይህ ወረርሽኝ፣ ሁሉንም የንግድ መስኮች እየነካካ ነው፡፡ በአንፃሩ ለአንዳድ ቢዝነሶችና አገልግሎቶች የዝማኔ በር እንዲከፈት ሰበብ እየሆነ ነው። በፋይናንሱ ዘርፍ በተለይ ባንኮች ላይ የቱንም ያህል ጫና ቢያሳርፍም፣ በሌላ አቅጣጫ ግን ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶች ላይ ትኩረት እንዲሠሩና ተጠቃሚዎችም ወደ ዘመናዊ አገልግሎት እንዲመጡ እያገዘ ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም። ከባንኮች ውጭ የሚደረግ ገንዘብ እንዲገደብ መደንገጉ ይታወቃል። ከዚሁ ጎን፣ በጥሬ ገንዘብ ባንክ ወደ ባንክ ማዘዋወርን ለማስቀረት አዲስ አሠራር እንዲተገበር መደረጉ ለባንኮች መልካም አጋጣሚ ሆኖላቸዋል።

  በመመርያውና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያነጋገርናቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ  ትኩረት ይደረግባቸው በማለት ያነሷቸው ነጥቦች አሉ። ባንኮች ቸገሩበት የነበረውን አሠራር በማስቀረት ከባንክ ወደ ባንክ ገንዘብ እንዲተላለፍ መፈቀዱ ለፋይናንስ ዘርፉ ትልቅ ለውጥ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ከአንድ ባንክ ወደ ሌላ ባንክ ገንዘብ ማስተላለፍ በግድ በጥሬ ገንዘብ ወጪ አድርጎ ቆጥሮና አስተካክሎ በጠባቂዎች አጀብ ወደ ሌላኛው ባንክ ማጓጓዝን ጠይቅ ነበር። ይህ አሠራር ጊዜ ከመፍጀቱም በላይ ለከፍተኛ ሥጋት የተጋለጠ ነበር፡፡ ባለሙያው በተቀየረው አሠራር መሠረት ጥሬ ገንዘብ በማጓጓዝ ሒደት የነበረውን ሥጋት የሚያስቀር ከመሆኑም በላይ ወጪ ቆጣቢ ነው ብለውታል።

  የኢኮኖሚስቱን ሐሳብ የሚጋሩት የዳሸን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ፣ዘመናዊ አገልግሎትን ከማስፋፋት ባሻገር ባንኮች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡና ፈጠራ የታከለበት አሠራር ውስጥ እንዲገቡ ያግዛቸዋል። ‹‹መመርያ መውጣት ባንኮችን የአዲስ አሠራር ፈጣሪዎች ያደርጋቸዋል፡፡ ደንበኛዬ በጥሬ ገንዘብ ማውጣት ስለማይችል፣ ምን ዓይነት ተስማሚ አገልግሎት ላምጣለት ወደ ማለቱ ይገባሉ›› በማለት፣ ደንበኞችን ላለማጣትና ገንዘብ በዘመናዊ መንገድ እንዲገባ ለማስቻል ፈጠራዎች ላይ እንዲያተኩሩ ያስችላቸዋል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ አስፋው ይገልጻሉ፡፡

  በዚህ ብቻ አይወሰንም። ዘመናዊ ባንክ አገልግሎት እየሰፋና ሌሎች የክፍያ አገልግሎቶችም በዚሁ ሥርዓት እንዲገዙ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የገለጹት የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ሲሆኑ፣ ጥሬ ገንዘብ ከባንክ ወደ ባንክ የማዘዋወሩ አሠራር እስካለፈው ሳምንት ድረስ ሲሠራበት ቆይቶ አሁን ላይ ግን ማንኛውም ባንክ ከየትኛውም ባንክ ገንዘብ ለማዘዋወር ጥሬ ገንዘብ ማጓጓዝ  አይጠበቅበትም፡፡ ስለዚህ ባንኮች ላይ የነበረውን ጫና ከመቀነሱም በላይ ዘመናዊ አገልግሎቶችን ለማስፋት ያግዛል ብለዋል፡፡

  በጥቅሉ ሲታይ መመርያው ለግብይት ጥሬ ገንዘብ የሚጠቀመው ተገልጋይ እንዲቀንስ በማድረግ፣ ከጥሬ ገንዘብ ባሻገር ያሉ የክፍያ ዘዴዎችን ማምጣት ዓላማ እንዳለው አቶ አስፋው ጠቅሰው፣ ከደኅንነት አኳያ ያሉ ችግሮችን ለማስቀረት፣ ሥውር ወንጀሎችን ለመከላከል ጭምር ያግዛል ብለዋል። ከባንኮች ተጠቃሚነት አንፃር ማየት ካስፈለገም ምሳሌዎችን መጥቀስ እንደሚቻል አቶ አስፋው ማብራሪያ መረዳት ይቻላል።

  ባንኮች እንቅስቃሴ ከጥሬ ገንዘብ ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ ለዚያ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ሲያፈሱ መቆየታቸውንና የኦፕሬሽን ወጪያቸውም ከፍተኛ እንደሆነ፣ የገንዘብ መቁጠሪያ ማሽኖች ያውም በውጭ ምንዛሪ እየተገዙ እንደሚመጡ አቶ አስፋው ጠቅሰው፣ ሌሎች ወጪዎች ሲታከሉበት የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴ ለባንኮች ወጪ መባባስ ምክንያት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ችግሩ ምን ያህል እንደነበር ለመግለጽም በምሳሌ የጠቀሱት የብር ኖቶች በቀላሉ እያረጁ ተጨማሪ ወጪ ማስከተላቸውን ነው፡፡ በንክኪ ብዛት የብር ኖቶች ጥቂት ካገለገሉ በኋላ ስለሚበላሹ ዳግመኛ ለማሳተም ብቻም ሳይሆን፣ ለሰው ጤናም ጠንቅ እስከመሆን ይደርሳሉ ብለዋል፡፡

  ሌላው ቀርቶ አሮጌ የብር ኖቶችን ወደ ኤቲኤም ማሽኖች ለማስገባት አስቸጋሪ እንደሆኑና ማሽኖቹ አገልግሎት መስጠት ሲቸግራቸው ከሚታዩባቸው ችግሮች አንዱ አዳዲስ የብር ኖቶች እንደ ልብ ባለማግኘት አሮጌ ብሮች እየተከተተባቸው በሚፈጠር ብልሽት ጭምር ነው፡፡ ‹‹ማሽኑ እንዳይቆም ባንኮች ሻል ያለውን የብር ኖት እየመረጡ  ይስገቡበታል፤›› ያሉት አቶ አስፋው፣ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ሲቀንስ የብር ኖቶች እርጅናም እየቀነሰ ረዥም ጊዜ እንዲያገለግሉ ከማገዝ አልፎ፣ ለብር ኖቶች ኅትመት የሚወጣው የውጭ ምንዛሪም እንዲቀንስ ያስችላል ብለዋል፡፡ የመመርያው መውጣት ሌላም ጥሩ ጎን እንዳለው የሚናገሩት አቶ አስፋው፣ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ጋር ያያይዙታል፡፡

  ከኢትዮጵያ ባንኮች ጋር የሚሠሩ የውጭ ባንኮችና ሌሎች ዓለም አቀፍ  የፋይናንስ ተቋማት የኢትዮጵያ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ለችግር ተጋላጭ መሆኑን የሚጠቅሱትም በጥሬ ገንዘብ ላይ የተመሠረተውን የንግድና የግብይት ሥርዓት በማመላከት ነው፡፡ እስካሁን በነበረው ሒደት ለስርቆት የተመቻቸ እንደሆነ በመተቸት፣ አሁን ሥራ ላይ እንደዋለው ዓይነት መመርያ ቀደም ብሎ አለመኖሩ፣ የገንዘብ ዝውውሩ ለውጭ ኢንቨስተሮች የማይመች ሆኖ ቆይቷል ተብሏል፡፡ የመመርያው መውጣት የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር ሊያግዝ ይችላል በማለት አቶ አስፋው አስረድተዋል፡፡

  ከሁሉም በላይ ግን የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂን በአገር አቀፍ ደረጃ ለመተግበርም የብሔራዊ ባንክ መመርያ አጋዥ እንደሆነ አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከጠቅላላ ሕዝቧ 38 በመቶ ብቻ የባንክ ተጠቃሚ እንደሆነና 62 በመቶ ገና  ባንክ እንዳልተዋወቀ በማውሳት ይህንን ለመለወጥ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር መቀነስ እንዳለበት አመላክተዋል፡፡ በዚህ መመርያ መሠረት ከፋይም ሆነ ተከፋይ የግድ ወደ ባንክ መምጣት ስለማይጠበቅባቸው የባንክ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ሊያሳድገው ይችላል ብለዋል፡፡

  ከባንክ ውጭ ያለው ገንዘብም ወደ ባንክ መጥቶ በመደኛው ኢኮኖሚ ውስጥ ካልተንቀሳቀሰ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለውና የገንዘብ እጥረት ሊያመጣ ስለሚችል መመርያው መውጣት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ያጎላዋል ተብሏል።

   ሁሉንም ባንኮች በአባልነት የያዘው ‹‹ኢትስዊች›› መሠረተ ልማት ከአንዱ ባንክ ወደ ሌላው ገንዘብ በማቀናነስ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን የሚያስቀር አሠራር እንዲተገበር ያደርጋል፡፡ ይህ አሠራር እንዲዘረጋ ለረዥም ጊዜ ሲወተወት እንደቆየ የኢኮኖሚ ባለሙያው አስታውሰው፣ የባንክ ደንበኞችም በዚህ እንዲጠቀሙና የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን በኦላይንና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች መለወጥ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

  የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን የሚገድበው አሠራር ሥጋትን ከመቀነስ፣ ወጪን ከመቆጠብና ዘመናዊ አሠራርን ከማጎልበት በላይ፣ ባንክ ወደ ባንክ ገንዘብ ለማዘዋወር እንዲሁም ክፍያዎችን ለመፈ የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴን በመቀነስ ገንዘቡ ከባንክ  ሳይወጣ እንዲቆይ የሚያስችል መሆኑ ጠቀሜታ የጎላ እንደሚሆን ይጠበቃል

  አሠራሩ ከኩባንያዎች በተጨማሪ፣ የግል ገንዘብ ለማንቀሳቀስና ልዩ ልዩ ክፍያዎችን ያለ ጥሬ ገንዘብ ለመፈጸም የሚያግዝ ነው፡፡ ይህ ሲሆን፣ ወደ ባንክ የሚመጣውን የገንዘብ መጠን ሊቀንሰው ይችላል የሚሉ አስተያየቶች ቢደመጡም፣ ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያም ሆኑ አቶ አስፋው በዚህ አይስማሙም፡፡ እንደውም ወደ ባንክ የሚሄዱ ሰዎችን ያበራክታል ይላሉ

  ይህ ይባል እንጂ በጥሬው የተከማቸ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ከሰሞኑ ቤታቸው ውስጥ ገንዘብ ለማስቀመጥ የካዝና ሸመታ ላይ ተጠምደዋል እየተባለ ነው፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት ከባንክ ውጭ አለ ተብሎ የሚነገረው ከ113 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ የትም ሊቀመጥ አይችልም፡፡ ሰዎች አንድ ነገር መረዳት አለባቸው፡፡ በመመርያው መሠረት ገንዘብ ይንቀሳቀስ የተባለው ሥርዓት ባለው መንገድ ከባንክ ባንክ ክፍያ ይፈጸም ነው፤›› በማለት መመርያው ሕጋዊ የገንዘብ እንቅስቃሴ እንደማይገድብ አቶ አስፋው አመልክተዋል፡፡

  ካዝና ግዥ ላይ የተጠመደ ሰው አደጋ ላይ ይወድቃል በማለት አቶ አስፋው አስጠንቅቀዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ሕጉ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን በመገደብ ብቻ ሳይወሰን፣ ባንኮች ለብሔራዊ ባንክ የሚያቀርቡት ሌላው ጥያቄ፣ ከባንክ ውጭ ምን ያህል ገንዘብ መያዝና በሰዎች እጅ መገኘት እንዳለበት የሚደነግግ ሕግ እንዲወጣ እያሳሰቡ በመሆናቸው ነው፡፡ ‹‹ይህ ሕግ ወጥቶ ሲተገበር በድንገተኛ ፍተሻ ወቅት ከተቀመጠው  ገደብ በላይ በቤቱ ገንዘብ የተገኘበት ሰው ይወረስበታል ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡ በዚህ መሠረት ወደፊት ከባንክ ውጭ ያለውን ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው ለማስገባት የሚያግዝ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል የጠቆሙት አቶ አስፋው፣ ከዚህ በኋላ እንደሚወጣ የሚጠበቀው ሕግ በቤት የሚቀመጠውን የገንዘብ መጠን በይፋ ይደነግጋል ብለዋል፡፡

  ‹‹መንግሥት የመገበያያ ገንዘብን ድንገት ሊለውጠው ስለሚችል፣ አንድ ሰው በእጁ መያዝ የሚጠበቅበት ገንዘብ 100 ሺሕ ብር ቢሆንና የገንዘብ ለውጡ ሲደረግ ግን 200 ሺሕ ብር ቢገኝበት ገንዘቡን ሊወረስ ይችላል ወይም በተለወጠው ገንዘብ ሊቀየርለት የሚችለው 100 ሺሕ ብር ብቻ ይሆናል ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ሰዎች ቤታቸው ያስቀመጡትን ገንዘብ ወደ ባንክ ማስገባት እንደሚጠቅማቸው ማሰብ ይኖርባቸዋል ያሉት አቶ አስፋው፣ ሥራ ላይ የዋለው መመርያም እንዲህ ያሉ ለውጦች እንደማይቀሩ ጠቋሚ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

  ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከባንክ ወደ ባንክ በቀጥታ ገንዘብ የማስተላለፍ ዘዴ ሌሎች ጠቀሜታዎች እንዳሉት ያስታወሱት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ ከዚህ በኋላ የኦላይን የግብይት ሥርዓት እንዲሰፋ ተቋማትም ወደዚህ ሥርዓት በመግባት ግብይታቸውን እንዲለውጡ ያስችላቸዋል ይላሉ፡፡ ኩባንያዎች ማንኛውንም ምርቶቻቸውን በኦላይን በማገበያየት በባንኮች በኩል የገንዘብ ልውውጡ እንዲፈጸም ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

  ጥሬ ገንዘብ ለማዘዋወር የሚከፈለው የኢንሹራንስ ወጪ ከፍተኛ መሆኑ ጭምር ለባንኮች የወጣው መመርያ ትልቅ ዕፎይታ እየሆነ ነው፡፡ የባንኮች ወጪ ሲቀንስ፣ በከፍተኛነቱ ወቀሳ የሚቀርብበት የብድር ማስከፈያ ወለድ እንዲቀንስ ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

  በመመርያው ለመሥራት ሊቸገሩ የሚችሉ ደንበኞች እንደሚኖሩም ይጠበቃል፡፡ ይህ እየታየ እንደሚገኝ የጠቀሱት አቶ አስፋው፣ ጥሬ ገንዘብ ማዕቀብ እየተደረገበት በመሆኑ ወደ ዲጂታል ሥርዓት መግባት ግዴታ እየሆነ መምጣቱን መረዳት ያስፈልጋም ብለዋል፡፡

  ደንበኞች አሠራሩን እስኪለምዱትና ወደ መስመር እስኪገቡ ድረስ እንደሚቸገሩ ቢታሰብም፣ እንዲህ ያሉ ችግሮች ለፈጠራ ስለሚያግዙ፣ ባንኮች ደንበኞቻቸውን ለማቆየትና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ተስማሚና ቀልጣፋ አሠራር እንዲዘረጉ ይገደዳሉ፡፡ ይህ እያደረጉ ኅብረተሰቡንም በቴክኖሎጂ የዳበረ የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ በማድረግ ወጪ ቆጣቢ አሠራር እንደሚያሰፉ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡

  31 May 2020

  Read more
 • ግብፅ የተመድን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ በመጣስ የሶማሊያን ጦር ማስታጠቋ እንዳሳሰበው የሶማሌላንድ መንግሥት አስታወቀ

  በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ የተደቀነ ሥጋት በማለት የግብፅን ድርጊት ኮንኗል

  በዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫ ውስጥ የከረሙት ሶማሊያና ሶማሌላንድ ዳግመኛ ያገረሸ ቁርሾ ውስጥ የገቡት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የጣለውን ማዕቀብ በመጣስ ግብፅ ለሞቃዲሾ መንግሥት የጦር መሣሪያ ዕርዳታ መስጠቷን የሚያመላክቱ መረጃዎች በመውጣታቸው ነው፡፡

  ሪፖርተር ከሶማሌላንድ መንግሥት ምንጮች አማካይነት አፈትልኮ የወጣውን ደብዳቤ አግኝቷል፡፡ ይኸው ከጥቂት ወራት በፊት በሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር ተፈርሞ ለግብፅ መከላከያ ሚኒስቴር የተጻፈው ደብዳቤ፣ ርክክብ የተፈጸመባቸውን መሣሪያዎች ዝርዝር ያሳያል፡፡ የካቲት 21 ቀን 2012  (እ.ኤ.አ. ፌብሩዋሪ 29 ቀን 2020) የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር ሐሳን አሊ ሞሐመድ ለግብፅ መንግሥት በጻፉት ደብዳቤ፣ 50 አርፒጂ-7 ላውንቸሮች፣ 36 የአልሞ ተኳሽ ጠብመንጃዎች ከ1,000 ጥይቶች ጋር፣ እንዲሁም ሌሎች 13 ዓይነት በዝርዝር የጠቀሷቸው የጦር መሣሪያዎች እንደተረከቡ አረጋግጠዋል፡፡

  በዚህም መሠረት ብዛታቸው 1,200 ክላሽኒኮቭ (ኤኬ47) ጠመንጃዎች፣ 25 ፒኬኤም መካከለኛ አውቶማቲክ መሣሪያ ከ700 ጥይቶች፣ 175 ፒኬኤም ቀላል አውቶማቲክ መሣሪያ ከ700 ጥይቶች፣ 50 አርፒጂ-7 ላውንቸሮች፣ 36 ባለ 12.7 ሚሊ ሜትር ደሸከ (ዶሽቃ) ከባድ አውቶማቲክ መሣሪያዎች፣ ስድስት ባለ 82 ሚሊ ሜትር ሞርታር ከ550 ተተኳሽ ጥይቶች ጋር፣ እንዲሁም 12 ባለ 60 ሚሊ ሜትር ከባድ ሞርታሮች ከ636 ሽጉጦች ጋር ግብፅ ለሶማሊያ መከላከያ ሠራዊት መለገሷን ከደብዳቤው ለመረዳት ተችሏል፡፡  

  የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር የተደረገለት የጦር መሣሪያ ድጋፍ ለአገሪቱ የፀጥታ ሥራ ብቻ እንደሚውል፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ ለሽያጭ ወይም ላልተፈቀደላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች እንደማይተላለፍ በመግለጽ ለግብፅ መከላከያ ሚኒስቴር ጽፏል፡፡

  ይኼንን ተከትሎ የሶማሌላንድ መከላከያ ሚኒስትር አብዲቃኒ ሞሐሙድ አቲዬ በትዊተር ገጻቸው  የአፍሪካ ኅብረትን፣ ተመድንና የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሒን ጠቅሰው በጻፉት ማሳሰቢያ ግብፅና ሶማሊያን ኮንነዋል፡፡ የሶማሊያ መንግሥት ለዓመታት ተጥሎበት የቆየውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ አለማክበሩን ያወሱት የመከላከያ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የግብፅ መንግሥትም በሶማሊያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ሆን ብሎ በመጣሱ እንቃወመዋለን፡፡ ይህ ድርጊት በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ላይ ከፍተኛ ሥጋት ይፈጥራል፤›› ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

  በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ምን እንደሆነ ለማወቅ ሪፖርተር ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርቦ፣ የሁለቱ አገሮች ጉዳይ በመሆኑ ምንም ዓይነት ምላሽ መስጠት እንደማይችል አስታውቋል፡፡ ሚኒስቴሩ ይህን ይበል እንጂ፣ በቀጣናው የፀጥታና የደኅንነት ጉዳዮች ላይ የካበተ ተሞክሮ ያላቸው ባለሙዎች ግን፣ መንግሥት ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እያለዘበና ቸል እያለ የመጣውን የሁለትዮሽ የፀጥታ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጥበት ያሳስባሉ፡፡ ፖለቲካዊ አሠላለፎች መለወጣቸው የሰላምና መረጋጋት ችግሮች እንዳያስፋፋ ያስጠነቅቃሉ፡፡

  ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደርና ለመተናኮስ የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም የሚሉት የዘርፉ ተንታኞች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወታደራዊ ትብብሮችን በመመሥረት ሰበብ ከደቡብ ሱዳን ጋር፣ አሁን ደግሞ ከሶማሊያ ጋር በግላጭ የጦር መሣሪያ ድጋፍ ማድረጓ መልዕክት አለው ይላሉ፡፡

  ተመድ ከሶማሊያ በተጨማሪ በኤርትራ ላይ የጣለውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ከቅርብ ከሚከታተሉ ተቋማት አንዱ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ)፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክትትሉን እያቋረጠ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ከሁለት ዓመታት ወዲህም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር በኤርትራና በሶማሊያ ላይ በሚከተለው የፖለቲካ አሠላለፍ ለውጥ ምክንያት፣ እንዲህ ያሉ ጥሰቶች ለአደጋ እንደሚያጋልጡ ያስረዳሉ፡፡

  እ.ኤ.አ. ከ1991 ጀምሮ ከሶማሊያ በመገንጠል ራሷን የቻለች ነፃ አገር መሆኗን ያወጀችው ሶማሌላንድ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በይፋ ዕውቅና ባታገኝም፣ በተዘዋዋሪ ዲፕሎማሲያዊ ከ20 በላይ አገሮች ጋር ግንኙነት በመመሥረት እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡ በሞቃዲሾ መንግሥትና በሶማሌላንድ መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ አዲስ ያገረሸው አለመግባባት ወደ ቃላት መወራወር አምርቶ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ሁለቱን ወገኖች ለማሸማገልና በጠረጴዛ ዙሪያ ለማደራደር የጀመሩት ሙከራ መክሸፉ ይታወሳል፡፡

  በሶማሊያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እ.ኤ.አ. ከ1992 ጀምሮ የፀና ሲሆን፣ በየጊዜው እየታደሰና እየተጠናከረ በመምጣት ከሁለት ዓመታት በፊት በከፊል እንዲሻሻል ቢደረግም፣ አሁንም ድረስ ባለበት እንዲፀና ተመድ ወስኗል፡፡

  የጦር መሣሪያ ማዕቀቡ በሶማሊያና በኤርትራ ላይ እንዲፀና የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ሲወስኑ፣ ኢትዮጵያም በወቅቱ በተመድ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ተቀዳ ዓለሙ (ዶ/ር) አማካይነት የውሳኔውን አስፈላጊነት ካብራሩና ድምፅ ከሰጡ የ11 አባል አገሮች ተወካዮች መካከል ነበረች፡፡ ተመድ በሶማሊያ የሚገኘውን የሰላም አስከባሪ ጦሩን እ.ኤ.አ. እስከ ጁን 30 ቀን 2020 ድረስ እንዲቆይ መወሰኑ ይታወሳል፡፡   

  31 May 2020

  REPORTOR
  Read more

Latest Articles

Most Popular

google.com, pub-5833971792216939, DIRECT, f08c47fec0942fa0