‹‹የዜጎችን ሕይወት ማዳን የመጀመርያውና ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ በመጪው ዓመት ከፍተኛ ገንዘብ በመጠባበቂያነት እንይዛለን›› ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በገንዘብ ሚኒስቴር የፊሲካል ፖሊሲና የፋይናንስ ዘርፍ የተመለከቱ ጉዳዮችን በሚኒስትር ዴኤታነት እንዲመሩ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ተሹመው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ከመሆናቸው በፊት የብሔራዊ ፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን፣ የአሁኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በመተካት ነበር የመንግሥት ሹመትን ተቀብለው መሥራት የጀመሩት፡፡ ለአራት ወራት በኮሚሽነርነት የመሩትን ተቋም አስረክበው ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ከመጡ አንድ ዓመት ከስምንት ወራት በላይ ያስቆጠሩት ኢዮብ (ዶ/ር)፣ በግሉ ዘርፍ በርካታ ተሞክሮ ያካበቱና የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክን ሲመሩ የቆዩባቸው ጊዜያት ይታወሳሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሜሪላንድ በፖለቲካል ኢኮኖሚ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን የሠሩት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በዓለም አቀፍ ፖሊሲ በተለይም በዓለም አቀፍ የንግድ ፖሊሲ  ከጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የማስትሬት ዲግሪያቸውን በማግኘት በንድፈ ሐሳብ በተሞክሮም የዳበረ ልምድ አካብተዋል፡፡ በመንግሥት የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ላይ ሰፊ ሚና ያላቸው ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት መላውን ዓለም ባዳረሰው የኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ እየደረሰ ስላለው ጫና፣ እንዲሁም መንግሥት እየወሰዳቸው ስለሚገኙት የፖሊሲ ዕርምጃዎች ኢዮብ (ዶ/ር) ከሪፖርተር ጋር ያደረጉትን ቆይታ ብርሃኑ ፈቃደ አጠናቅሮታል፡፡

ሪፖርተር፡- በኮሮና ምክንያት ኢትዮጵያ ምን ያህል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎቿን ታጣለች?

ኢዮብ (ዶ/ር)፡- የኮሮና ወረርሽኝ ለየትኛውም ዓለም ኢትዮጵያን ጨምሮ ከባድ ፈተና ነው፡፡ ምን ያህል ፈተና ሊያመጣብን ይችል ነበር? ምን አጣን? ምንስ ተጎዳን? የሚሉትን ለያይቶ መመልከቱ ጠቃሚ ነው፡፡ በአጠቃላይ ወረርሽኙ በባህሪው የሰዎችን ማኅበራዊ መስተጋብር የሚከለክል ከመሆኑ አኳያ፣ በጤና በኩል ከሚመጣው ጉዳት በማያንስ በኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በሰዎች እንቅስቃሴ ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው ለጉዳት ተጋላጭ ናቸው፡፡ በአገልግሎት መስክ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስን ይጠይቃሉ፡፡ በምርት ሒደትም ሰዎች በጋራ ሆነው ይሠራሉ፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛና አሉታዊ ተፅዕኖ እየደረሰ ነው ያለው፡፡ በመሆኑም ጉዳቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ደጋግመን እንደምንገልጸው ይህንን ጉዳት በመረዳት ገና ከጅምሩ የኮሮና ምላሻችን በጥንቃቄ የተዘጋጀ፣ የዜጎችን ሕይወትና ኑሯቸውን የጠበቀ ምላሽ መስጠት አለብን የሚል አቋም ስለነበረን ብዙ ርቀት ሊያስኬደን የሚችል ስትራቴጂ የዘረጋን ይመስለኛል፡፡ በዚህ መንገድ ምላሽ የምንሰጥበት ስትራቴጂ ባይኖረን ኖሮ ጉዳቱ ከባድና በኢኮኖሚው ላይም ዘለቄታዊ ጉዳት አድርሶ ይሄድ ነበር፡፡ አሁን እንደሚታየው በመጠኑም ቢሆን ደህና በሚባል ሁኔታ እየተቋቋምን ነው፡፡ ምርታማ ዘርፎችን በነበሩበት መንገድ እያመረቱ እንዲቆዩ ማድረግ አማራጭ የለውም፡፡ ግምገማውን ስናየው የምግብ ዕርዳታ የሚፈልግ 15 ሚሊዮን ተጨማሪ ሰው ከተፈጠረ፣ በርካታ ዜጎች ለሥራ አጥነት የሚዳረጉ ከሆነ፣ እነዚህ ችግሮች እንዳይፈጠሩ የምንወስደው ዕርምጃ ችግሮቹ ከመጡ በኋላ ከምንወስደው ዕርምጃ ይልቅ ትልቅ ውጤት ስለሚኖረው በዚያ መንገድ ምላሽ እየሰጠን ነው፡፡

በሥራ አጥነት ላይ የተሠራው ትንበያ አሳሳቢ ነበር፡፡ ነገር ግን የሰጠነው ምላሽ ተቋማት እንዴት አድርገው ሠራተኞቻቸውን ይዘውን ያቆዩ? ወደሚል የፖሊሲ ምላሽ በመሄድ መንግሥትም ይህንን የሚያግዙ የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ ነው፡፡ ተቋማት እንዳይሞቱና የዜጎች ህልውና፣ ደኅንነታቸውና ኑሯቸው እንዲጠበቅ ምን እናድርግ በሚለው መንገድ የሄድነው፡፡ ተቋማት ሠራተኞቻቸውን እንዳይበትኑ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መከልከል ብቻ ሳይሆን፣ ይኼንን በፖሊሲ እንደግፍ ብለን ለምሳሌ በጣም ከተጎዱት መካከል ዋናው የቱሪዝምና የሆቴል ዘርፍ እንደ መሆኑ መጠን፣ በዘርፉ ያሉትን ተቋማት ሠራተኞቻቸውን ማቆየት እንዲችሉ ምን እናድርግላችሁ ብለን በምክክር ሐሳባቸውን ለመረዳት ሞክረናል፡፡ እነሱም አፋጣኝ የአጭር ጊዜ ብድር ካገኘንና የብድር ዕዳዎቻችን ከተሸጋሸጉልን ችግሩ መቼ እንደሚያበቃ ባይታወቅም ማለፍ እንደሚቻል ሐሳብ ስላቀረቡ በዚሁ መንገድ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ ይህ ችግር ካለፈ በኋላም በቶሎ አገግመን ወደ ሥራ የምንገባው በእጃችን ያለ ሠራተኛ ሲኖር ነው፡፡ ያልበተነው ሠራተኛ ሲኖር፣ ስናሠለጥነው የቆየነው ሠራተኛ ለሥራ ዝግጁ ሆኖ ሲገኝ ወደ ሥራ በቶሎ መግባት ቀላል ይሆናል፡፡

ሌላው ጉዳይ ግብርናን ጨምሮ አምራቹ ዘርፍ ተጨማሪ ግብዓት እያመጣ ነው ወይ? ገበሬውስ አስፈላጊውን ርቀት ጠብቆ በሥራው ላይ ነው ወይ? የሚሉትን ስናይ አዎን የምርት ሥራ እንዳይቋረጥ አድርገናል፡፡ ገበሬው የምርት ግብዓቶች በቶሎ እንዲያገኝ፣ ከዚህም አልፈን የምግብ ዕጦት ሥጋት ሊኖር ስለሚችልና የዓለም የአቅርቦት ሰንሰለትም ችግር ውስጥ መውደቁ ስለሚያሠጋ፣ በአገራችን ያለውን ምርት ማሳደግ አለብን በማለት የተለዩና ከዚህ ቀደም ያልነበሩ አዳዲስ አሠራሮችን ተከትለናል፡፡ ለምሳሌ ለገበሬው የውኃ መሳቢያ ፓምፕ ማሠራጨት በዕቅድ ያልነበረ ነው፡፡ ወደ ሥራ ያልገቡ መስኖዎችን በቶሎ አጠናቆ ወደ ሥራ ማስገበት ሌላኛው ዕርምጃ ነው፡፡ የማንም መሬት ፆም እንዳያድር፣ በስኳር ኮርፖሬሽንና በክልሎች መካከል  የባለቤትነት ጥያቄዎች ያሉባቸው፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በዕዳ የያዛቸውና ሌሎችም ባሉበት ሆነው ፆም ሳያድሩ ምርት እንዲመረትባቸው፣ ያሉትን ችግሮች ግን ዋል አደር ብለን እንነጋገርባቸዋለን በማለት ወሳኝ የፖሊሲ ዕርምጃ ወስደናል፡፡

ጉዳቱ ከመጣ በኋላ ለመቋቋም ከምናደርገው መረባረብ ይልቅ፣ ሳይመጣ ቀድመን ምላሽ መስጠት የምንችልበትን አቅም መገንባት ላይ ያተኮርነው፡፡ በአጠቃላይ በኢኮኖሚው ላይ ጉዳት አለ፡፡ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) እስከ ሦስት በመቶ ቅናሽ እንደሚኖር ግምት ወስደናል፡፡ ደግነቱ ግን የእኛ በጀት ዓመት ከውጮቹ የተለየ በመሆኑ፣ የበጀት ዓመቱን የዘጠኝ ወራት ገደማ ሥራ በጨረስንበት ወቅት ነው ወረርሽኙ የመጣው፡፡ ከዚያ በፊት በነበሩት ጊዜያት የመንግሥት ገቢ መቶ በመቶ በሚባል ውጤት ደረጃ ስንሰበስብ ቆይተናል፡፡ ጉዳቱ የመጣው በተቀሩት ወራት ወቅት እንደ መሆኑ፣ የጉዳቱ መጠንም በመጨረሻው ሩብ ዓመት ላይ በሚደርሰው መጠን የሚለካ ይሆናል፡፡ በዓለም ላይ ያደረሰው ጫናም ተደምሮ የሦስት በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ጉዳት ማድረሱ በጣም ትልቅ ተፅዕኖ ነው፡፡ እስካሁን የማገገሚያ ዕቅዱ ከአደጋ ጊዜ ምላሽ አሰጣጥ ዕቅድ ጋር ተዛምዶ እንዲሄድ መደረጉ በብዙ የረዳን ይመስለኛል፡፡ ጥሩ ውጤት ያስገኘ ስትራቴጂ እንደተከተልን አስባለሁ፡፡       

ሪፖርተር፡- እስከ ሦስት በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ቅናሽ እንዲመዘገብ የኮሮና ወረርሽኝ ስለሚያስገድድ በንግድ ሚዛንና በክፍያ ሚዛን ጉድለት ላይ፣ በውጭ ሐዋላ ገቢና በሌሎችም መስኮች ላይ የሠራችኋቸው ትንበያዎች አሉ?

ኢዮብ (ዶ/ር)፡- ችግር የሆነብን ትንበያው በየቀኑ ተለዋዋጭ እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡ መጀመርያ ላይ ለልማት አጋሮች ድጋፍ በሚል በሠራነው ሥራ ላይ ያስቀመጥናቸው ትንበያዎች የውጭ ሐዋላ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጎዳ፣ በኢንቨስትመንት ፍሰትም ላይ እስከ 40 በመቶ ቅናሽ ሊመዘገብ እንደሚችል፣ በወጪ ንግድ ላይ ያስቀመጥናቸው ትንበያዎች አሉ፡፡ በሌላ በኩል በመከላከል ሥራ ላይ የተከተልነው ስትራቴጂ ያመጣቸው ውጤቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ በቡና ወጪ ንግድ ላይ ከጠበቅነው በላይ ማንሰራራት ተመልክተናል፡፡ አንዳንድ አገሮች ከገመትነው ጊዜ ቀድመው ድንበሮቻቸውን በመክፈታቸው የአበባ የወጪ ንግድም በመጠኑ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ በመሆኑም ቀድመን ያወጣናቸውን ትንበያዎች እንደገና መከለስ ሊኖርብን ነው፡፡ አጠቃላይ ጉዳቱ ምን ያህል እንደሚሆን ለማወቅ በጀት ዓመቱ ካለቀ በኋላም ቢሆን ተመራጭ ነው፡፡ በየሳምንቱ እየተቀያየረ ባለው የትንበያ ሁኔታ ላይ ጊዜ ማጥፋት ብዙም ጠቀሜታ አይኖረውም፡፡ ይሁን እንጂ የሐዋላ ገቢና የኢንቨስትመንት ፍሰት በመቀነሱ፣ ወይም ገንዘባቸውን እዚህ ለማምጣት ወስነው የነበሩ ኩባንያዎች በተለያዩ ችግሮች ተይዘው ይገኛሉ፡፡ ኢንቨስትመንት የሚለካው ውሳኔ ለተሰጠበት የሥራ መስክ የሚያስፈልገው ገንዘብ እዚህ መጥቶ ሲመዘገብ ነው፡፡ እነዚህ መቀነሳቸው አልቀረም፡፡ በሌላ በኩል ከነዳጅ የምናገኘው የዋጋ ዕፎይታ ይኖራል፡፡ በገቢ ንግድ ረገድ ወሳኝ በሚባሉት ላይ ለምሳሌ የሕክምና አቅርቦቶች በምንም መንገድ አይቀንሱም፡፡ ማዳበሪያና ምግብ ነክ ሸቀጦች ቅድሚያ አግኝተው እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ በግሉ ዘርፍ አማካይነት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሸቀጦች መቀነሳቸው አይቀርም፡፡ በተለይም ቅድሚያ የማይሰጣቸው ሸቀጦች ብዙም ትኩረት ላያገኙ ይችላሉ፡፡ በጠቅላላው ግን አሁን ትንበያዎችን መሥራት ትተናል፡፡ ቀድሞ በተሠራው ላይ ሊኖሩ የሚችሉ ለውጦችን እያየንና እያስተካከልን፣ በዓመቱ መጨረሻ ላይ የደረሰውን ጉዳት አጣምረን ሪፖርት እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ሁኔታ የኮሮና ወረርሽኝ በከፍተኛ መጠን ይስፋፋል ተብሎ የተተነበየው ከሰኔ ወር በኋላ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የተለየና ለአደጋ ጊዜ ተብሎ የተዘጋጀ የመጠባበቂያ በጀት አለ?

ኢዮብ (ዶ/ር)፡- አዎን፡፡ በዚህ ዓመት እንኳ ካየን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያፀደቀው የበጀት ማስተካከያ አለ፡፡ ይኼ በሰፊው ለምን አስፈለገ ከተባለ ወጪያችን በከፍተኛ መጠን ጨምሮ ገቢያችን እየቀነሰ በመምጣቱ ነው፡፡ ወጪያችን እንዴት ጨመረ ካልከኝ፣ በሽታውን ለመከላከል የምናወጣቸው ትልልቅ ወጪዎች ስላሉ ነው፡፡ ለጤና መስክ ብቻ በጤና ሚኒስቴር የተጠየቀው በየጊዜው የሚወሰድ 15 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል፡፡ ለአደጋ መከላከል ሥራው በተለይም በቂ ምግብ ለማቅረብ የሚወጣ ወጪ አለ፡፡ በቅርቡ 600 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለመግዛት ጨረታ መውጣቱ ይታወቃል፡፡ ተቋማትን ለመደገፍ ለምሳሌ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች፣ ለኅብረት ሥራ ማኅበራትና ለአነስተኛ ገንዘብ አቅራቢ ድርጅቶች በልማት ባንክ በኩል 4.5 ቢሊዮን ብር ድጋፍ እንዲያገኙ ተወስኗል፡፡ ይህ ሁሉ ያልታሰበ ተጨማሪ ወጪ ነው፡፡ እነዚህን በገንዘብ ለመደገፍ የፊስካል በጀት ማስተካከያ ማድረግ አስፈልጎናል፡፡ በገቢ ደረጃ የጠበቅነው አልተገኘም፡፡ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ያገኘነው ድጋፍ ቢኖርም ለተጨማሪ ብድር መሄዳችን አይቀርም፡፡ ተጨማሪ የበጀት ማስተካከያ እንዲፀድቅ ከመጠየቃችን በተጨማሪ የመጪው በጀት ዓመትም ትኩረት ይሰጠዋል፡፡

በነገራችን ላይ ሁሉም ሰው እየገመተ እንጂ፣ የበሽታው ሥርጭት የሚባባሰው በትክክል ሰኔ ላይ ወይም ሐምሌ ላይ የመሆኑ ነገር በትክክል አይታወቅም፡፡ በታቸለ መጠን መንግሥት በዕውቀት ላይ በተመሠረተ ዕቅድ መመራት ስላላበት፣ በዓለም ላይ ያሉ ምሁራንን ከኢትዮጵያውያን ጋር አካተን፣ የሳይንሳዊ አማካሪ ቡድኑን ጨምረን የበሽታው ጉዳት እየበሳ የሚመጣው መቼ እንደሚሆን ለመተንበይ ተሞክሯል፡፡ አሳሳቢው ጊዜ ገና ከፊታችን እንደሚመጣ ሥጋቱ አለን፡፡ ሥጋቱን ዝቅ አድርጎ መመልከት አይቻልም፡፡ ጉዳቱ መቼ ነው የሚከሰተው የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ አሳሳቢ ጊዜ እንደሚጠብቀን ግልጽ ነው፡፡ እንደ ንሥር ዓይናችንን በሽታውን ከመከላከሉ ሥራ ላይ ሳንነቅል፣ የተጠናከረ ዝግጅት ማድረግ እንዳለብን የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ አኳያም የመጪው በጀት ዓመት ይህንን ከግምት የከተተ ዝግጅት የተደረገበትና ከእስካሁኑ ጥብቅ የወጪ ፖሊሲ አኳያ እንዲላላ የሚደረግበት የአደጋ ጊዜ ምላሽ መስጫ ዕቅድ ይኖረናል፡፡ የዜጎችን ሕይወት ማዳን የመጀመርያውና ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ፣ በመጪው ዓመት ከፍተኛ ገንዘብ በመጠባበቂያነት እንይዛለን፡፡ በጀቱም ከተመለደው አካሄድ ከ60 እስከ 70 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ኖሮት ይዘጋጃል፡፡ የሪፎርም ሥራችን በዚህ ጊዜም ስለማይቆም የገቢ መሰብሰብ አቅማችንን በማሻሻል እንሠራለን፡፡ የበጀት ጉድለቱ ቢሰፋም ባይሰፋም፣ ሰፊ የፊስካል በጀት ይኖራል፡፡

ሪፖርተር፡- ለተጨማሪ በጀት የጠየቃችሁት የገንዘብ መጠን ምን ያህል ነው?

ኢዮብ (ዶ/ር)፡- ለፓርላማው ቀርቦ እንሚፀድቅ የሚጠበቀው ተጨማሪ በጀት 48.5 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህን ገንዘብ የጠየቅነው የታየውን የገቢ ቅናሽ ለማካካስ ጭምር ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት በታክስ ምሕረትና ዕፎይታ እስከ 78 ቢሊዮን ብር ገቢ ሊያጣ የሚችልበት አጋጣሚ እንደሚኖር አስታውቀው ነበር፡፡ በታክስ ምሕረቱ ላይ በተለይ እስከ 2007 ዓ.ም. የተከማቸው የአሥር ዓመታት የታክስ ዕዳ በመንግሥት ድክመት ጭምር ካለመሰብሰቡ አኳያ፣ እንድ ድጋፍ ሊቆጠር አይገባም የሚሉ አጨቃጫቂ ጉዳዮች ሲነሱ ሰምተናል፡፡ ይህንን እንዴት ነው ያያችሁት?

ኢዮብ (ዶ/ር)፡- በደንብ በዝርዝር ነው ያየነው፡፡ ከጠቅስከው ውስጥ እስከ 68 ቢሊዮኑን ብር በተሰብሳቢ ሒሳብ ውስጥ የነበረ ገንዘብ ነው፡፡ አንዳንዱ እንደጠቀስከው ለዓመታት ሳይሰበሰብ የቆየ ነው፡፡ በክርክር ሒደት ላይ ያሉና ትኩስ፣ በኦዲት የወጡ አዳዲስ ሒሳቦችም አሉ፡፡ ደረጃቸው ይለያያል፡፡ ማየት ያለብህ ነገር የተሰብሳቢ ሒሳቦች ተፅዕኖ ነው፡፡ ተቋማት በዚህ ዕዳ የተነሳ ወይ ንብረታቸው ተይዞባቸዋል ወይም የባንክ ሒሳባቸው ተዘግቶባቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ማከናወን ተስኗቸዋል፡፡ የእኛ የአደጋ ጊዜ ምላሽ የዜጎችን ሕይወትና ኑሯቸውን መጠበቅ ነው ካልን፣ እንዲሁም አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ተጋላጭ ሳይሆን እንደነበረ እንዲቆይ ማድረግ ከመሆኑ አኳያ፣ በታክስ ክርክር ምክንያት ዕግድ ውስጥ የሚገኝ፣ ንብረቱ የተያዘበት፣ የባንክ ሒሳቡ የተዘጋበትን ተቋም ከዚህ ክርክር አውጥተህ ወደ ሥራ እንዲመለስ አደረግኸው ማለት ሰዎች ዳግም ሥራ እንዲያገኙ፣ ተጨማሪ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖር ዕድል ፈጠርክ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በጣም ትርጉም ያለው ድጋፍ ነው፡፡ ድጋፍ አይደለም ለሚሉ ሰዎች ድጋፉን ያገኙትን ሰዎች ሄዶ መጠየቅ ነው ያለባቸው፡፡ እነሱ ናቸው ምን ያህል ትልቅ ዕፎይታ እንዳስገኘላቸው ሊገልጹ የሚችሉት፡፡ የእኛ ግምገማ ግን ለግሉ ዘርፍ ትልቅ ዕፎይታ የሰጠ ዕርምጃ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ የመንግሥትን ገቢ ያሳጣል ወይ ከተባለ ያለ ምንም ጥርጥር አዎ፡፡ ነገር ግን ዛሬ የምናጣው ገቢ ሳይሆን እነዚህ ተቋማት አገግመውና ወደ ሥራ ገብተው፣ በመጪው ዓመትና ከዚያ በኋላ የምናገኘው የታክስ ገቢ ብሎም ሰዎች ሥራ አግኝተው መኖራቸው የሚያስገኘው አገራዊ ጥቅም ይበልጣል በማለት ነው ድጋፉን የሰጠነው፡፡ ትልቅ ትርጉም ያለው ድጋፍ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የቱሪዝምና የሆቴል ዘርፍ ያገኘውን ድጋፍ ጠቁመው ነበር፡፡ ጥያቄያችን በከፊል ምላሽ አግኝቷል እያሉ ነው፡፡ የብድር ክፍያ ወደ አንድ ዓመት ይራዘምልን የሚለው ጥያቄያቸው የመንግሥትን ምላሽ እየጠበቀ እንደሚገኝ በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ ማኅበራት እየተናገሩ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ የሰጣችሁት ምላሽ ምንድነው?

ኢዮብ (ዶ/ር)፡- ይህንን ጥያቄ በዝርዝር ነው ያየነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም ከዘርፉ አመራሮች ጋር ውይይት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ መጀመርያ አካባቢ የነበረው ዕሳቤ ባንኮች የነበረባቸው የገንዘብ ችግር ከተፈታ፣ የተቋማቱን ብድር የማራዘም ወይም ተጨማሪ ብድር የመስጠት ሥራ ይሠራሉ የሚል ነበር፡፡ አንዳንድ ባንኮች ሙሉ በሙሉ ለዚህ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በተለይ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ያሉት ጥያቄያችን አልተመለሰም፣ ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልገናል የሚል ጥያቄ በማቅረባቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ አመራሮች ይህንን ጥያቄ ዳግመኛ ተመልከተው፣ እነዚህ ተቋማት አስቸኳይ የአጭር ጊዜ ብድር እንዲያገኙ ተመቻችቶላቸዋል፡፡ ብድሩንም እየወሰዱ ነው፡፡ ጥያቄያቸው በተለየ መንገድ ነው ምላሽ ያገኘው፡፡ የባንኮች ፕሬዚዳንቶችንና የባንኮች ቦርድ ኃላፊዎችን ባካተተ ውይይት፣ ብሔራዊ ባንክ ከሚያስተላልፋቸው ትዕዛዞች ይልቅ ከባንኮች የሚመጣው መፍትሔ ይሻላል የሚል አሳታፊ መፍትሔ በመከተል፣ ከባንኮች በመጣ የመፍትሔ ሐሳብ መነሻነትም ጭምር ነው ምላሽ የተሰጠው፡፡ በበሽታው ተፅዕኖ እስከ ስድስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ሊፈታ የሚችል ድጋፍ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የቱሪዝም ዘርፉ ካልተነቃቃ አብረን የምናየው ነው፡፡ ነገር ግን የምንሰጠው የኢኮኖሚ ድጋፍ ከጉዳቱ ጋር ተመጣጣኝ መሆን አለበት የሚል ጠንካራ አቋም አለን፡፡ ለስድስት ወራት ከሆነ ሥራ የሚቆመው ለዚህ ጊዜ የሚሆን ብድር ይቀርብና ሥራ ሲጀመር ብድሩም መከፈል ይጀምራል ማለት ነው፡፡ ባንኩም ቢሆን ተጨማሪ ብድር መስጠት የሚችለው ገንዘቡ ሲመለስለት ነው፡፡ በጠቅላላው ግን የቱሪዝም ዘርፉ ጥያቄ ተመልሷል ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- የአገሪቱ ኢኮኖሚስቶች፣ የእናንተ መሥሪያ ቤት፣ እንዲሁም የዓለም ገንዘብ ድርጅት ልዩ ልዩ የሥጋት ትንበያዎችን ሲያወጡ ከርመዋል፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ የብድር መሸከምና መክፈል አቅምን የሚለኩ ተቋማት ከዚህ ቀደም የነበረውን የአገሪቱን ደረጃ ዝቅ አድርገዋል፡፡ አንዱ መነሻቸው አገሪቱ ያለባትን የገንዘብ ችግር፣ እንዲሁም ዕዳ ለመክፈል እንደሚያዳግታት የሚያሳዩ መረጃዎች ናቸው፡፡ የተቋማቱን ሪፖርቶች ተመልክታችኋል?

ኢዮብ (ዶ/ር)፡- ዓይተናቸዋል ግን ብዙም አላሳሰቡንም፡፡ ኢትዮጵያን ብቻም ሳይሆን፣ በአጠቃላይ አገሮች ናቸው የታዩት፡፡ ደረጃችን ዝቅ ሊደረግ የቻለው በምን መነሻ ነው የሚለውን ማየት ነው፡፡ እነዚህ አገሮች ያለባቸውን ብድር መክፈል አይችሉ ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት አጠቃላይ የብድር አቅም መመዘኛ አመላካቾች ወደ ኔጋቲቭ ዝቅ የተደረጉበት ዋናው ማጠንጠኛ ምክንያት፣ የብድር ዕዳቸውን አይከፍሉ ይሆናል የሚል ነው፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት መንግሥታት ያነሱት ጥያቄ አለ፡፡ በወረርሽኙ ሥጋት ምክንያት ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይሻለናል፣ የዜጎችን ሕይወት የማዳን ተግባር ቅድሚያ ማግኘት አለበት፣ የብድር ክፍያ ይራዘም የሚል ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ በዚህ ምክያት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የአፍሪካ ድምፅ ሆኖ በቀረበው ጥያቄ መሠረት፣ የቡድን 20 አባል አገሮች ለዘጠኝ ወራት ብድር ሳይከፈል እንዲቆይ የሚያስችል ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ ይህ ጥሪ በቂ ግን አይደለም የሚል ክርክር እያነሳን ነው፡፡ በመሆኑም ተቋማቱ ያወጡት የክሬዲት ምዘና በአብዛኛው የተገኘው አገሮች ያለባቸውን ብድር ላይከፍሉ ይችላሉ ከሚል ሥጋት ነው፡፡ ይህንን ያዩ አገሮች ለምሳሌ እነ ኬንያ ከገበያ ላይ ብድር ስለሚያገኙ ሊመጣባቸው የሚችለውን ሥጋት በመገንዘብ፣ አንከፍልም አላልንም በማለት መግለጫ አውጥተዋል፡፡ እኛ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው አንድ ዩሮ ቦንድ ነው ከብድር ገበያ ያገኘነው፡፡ የሬቲንግ ኤጀንሲዎቹ ሥጋት ብድር ላይከፈል ይችላል የሚል በመሆኑ እኛን ብዙም አላሳሰበንም፡፡ የበሽታው ጫና መስመር ሲይዝና ነገሮች ሲስተካከሉ፣ ያወጡትን ደረጃ መልሰው እንደሚያሻሽሉት የሚጠበቅ በመሆኑ ብዙም አላሳሰበንም፡፡ ከእነሱም ጋር ተነጋግረንበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰሞኑ መነጋገሪያ ከነበሩት አንዱ የዓለም ገንዘብ ድርጅት እንደ ወትሮው ሁሉ፣ በዚህ ወቅት የወለድ ምጣኔ የሚመራበት አግባብ ቁጥጥር ከሚደረግበት አሠራር ወጥቶ በገበያ እንዲመራ ይደረግ የሚለውን ጨምሮ፣ አሁንም የምንዛሪ ተመን ላይ ማሻሻያ ወይም ቅናሽ ይደረግ የሚል ጥያቄ ማቅረቡ ነው፡፡ ከተቋሙ ጋር ስለነዚህ ጉዳዮች ተነጋግራችኋል?

ኢዮብ (ዶ/ር)፡- እነዚህ ጉዳዮች ብዙ ጊዜ ይነሳሉ፡፡ አዲስ አይደሉም፡፡ ትልቁ ነገር እኛ እንደ መንግሥት የያዝነው የሪፎርም አቅጣጫ አለ፡፡ በሦስት ዓመታት ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚውን መዛባቶች አጥርተን እንጨርሳለን ብለናል፡፡ ሪፎርማችን ግን ቁንጽልና በፋይናንስ ዘርፉ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አይሆንም፡፡ የአምራች ዘርፉን እናነቃቃለን፣ የኢኖሚውን መዋቅራዊ ችግሮች እንፈታለን ብለን የያዝነው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አለን፡፡ በዚያ ማዕቀፍ ነው ሁሉንም ነገር የምናየው፡፡ ሐሳቦች ሲነሱ እንሰማለን፡፡ የጠቀመንን እንወስዳለን፣ የማይጠቅመንን እንተዋለን፡፡ ይህ ነው አካሄዳችን፡፡ የተናበበ የማክሮ፣ የዘርፍና የመዋቅር ለውጥ ግን ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ የሚወሰዱት ኢኮኖሚያዊ ዕርምጃዎችም መሠረታዊ የኢኮኖሚ መርሆዎችን የሚከተሉ መሆን አለባቸው፡፡ ከዚህ በፊት እንዳደረግናቸው ዓይነት በግማሽ የበሰሉ በግማሹ ጥሬ የሆኑ መፍትሔዎችን አንተገብርም፡፡ ለምሳሌ የ15 በመቶ የምንዛሪ ለውጥ አድርጋለሁ ስትል፣ ለዚህ ተመጣጣኝ የሆነ ሥራ በአምራች ዘርፉ ላይ ካልሠራህ የወጪ ንግድ ዘርፉ ምላሽ አይሰጥህም፡፡ ስለዚህ እንደ መንግሥት እንዲህ ያለ ያልተናበበ የፖሊሲ ዕርምጃ አንወስድም፡፡ እዚህ ላይ ጠንካራ አቋም አለን፡፡ ማንኛውም ሰው የመሰለውን ሐሳብ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ የሚጠቅመውን መውሰድ፣ የማይጠቅመውን ለምን እንደማይጠቅም ማስረዳትና መተው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዓለም ከኮሮና ማገገሚያና ድጋፍ ዕርምጃዎች ወደ ኮሮና ተፅዕኖ መውጫዎች ያተኮሩ መፍትሔዎች ላይ ትኩረት እየተደረገ ነው፡፡ በኢትዮጵያስ ምን እየተደረገ ነው? ከቀውሱ የሚወጣበት ስትራቴጂስ ምንድነው? 

ኢዮብ (ዶ/ር)፡- ስትራቴጂ አለን፡፡ ነገር ግን የቀውስ ጊዜ ለብቻው የማገገሚያ ጊዜና ቆይቶ ለብቻ የሚመጣ ስትራቴጂም አንከተልም፡፡ ደጋግመን አብሮ መሄድ አለበት፣ መናበብ አለበት የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ቀውሱ ካለፈ ከስድስት ወራት በኋላ እንደ አዲስ የምናስብበት የኢኮኖሚ ማገገሚያና ከቀውስ መሻገሪያ ዕቅድ ሳይሆን፣ አንዱ ከሌላው አብሮ የሚሄድ ስትራቴጂ ነው የምንከተለው፡፡ የዜጎችን ደኅንነትና ኑሯቸውን የመጠበቅ ሥራ ተቋማት እንዳይሞቱ አብሮ ከመጠበቅ ጋር አብሮ እየተሠራበት ያለ ነው፡፡ ጥያቄው መቼ ነው ይህ ቀውስ አልፎ ስለሌሎች ጉዳዮች የምንነጋገረው ከሆነ፣ እውነት ለመናገር ቀውሱ መቼ እንደሚያበቃ አናውቀውም፡፡ በእርግጠኝነት የምናውቀው ነገር ቢኖር የምንከተለው ስትራቴጂ እየሠራ መሆኑን ነው፡፡ ለጤና አጠባበቅ የሚመከሩና የሚተገበሩ ሥርዓቶችን እያስጠበቅን፣ ቁልፍ የኢኮኖሚ ክፍሎች በበሽታው ሳቢያ እንዳይስተጓጎሉ እያደረግን ነው፡፡ በእኛ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ሥራ በማስቆምና እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ እንዲገታ የማድረግ ዕርምጃ አንከተልም፡፡ አሁንም በዚሁ መንገድ እንቀጥላለን፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ቦታዎች ከፍተኛ የበሽታው ተዛምቶ ከታየ እነሱን ለይቶ በመዝጋት የሚከናወን ሥራ ይኖራል፡፡ በአዲስ አበባ በየትኞቹ ቦታዎች ከፍተኛ መስፋፋት ሊታይ እንደሚችል የሚያሳይ ጥናት ተካሂዷል፡፡ ቢሳካልን ኖሮ ሰው የፈራውን ያህል ፈርቶ፣ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረገና መመርያዎችን እያከበረ በተገቢው መንገድ ራሱን ጠብቆ ሥራውን እየሠራ ቢገባ፣ በሽታውን ከዚህም በላይ ልንከላከለው እንችል ነበር፡፡ በየመንደሩ ስንወርድ የግንዛቤውና የጥንቃቄ ትግበራው ላይ ብዙ ጥረትም ተደርጎ ችግሮች አሉ፡፡ በሽታው እየባሰ በመምጣቱ ግን አሁን ወደ ሕግ ማስከበር ዕርምጃዎች እየተገባ ነው፡፡ መቼ ነው ወረርሽኙ አልፏል ብለን የምናውጀው ከተባለ አናውቅም፡፡ ያንን ያወቅን ዕለት ዜናውን ከሰማን ቀድመን እናበስራችኋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ሁኔታ እስከ ክረምት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው ትልቁ ፍራቻ ያለው፡፡ ከክረምቱ መግባት በፊት የሚጠበቅ ነገር አለ?

ኢዮብ (ዶ/ር)፡- በፍላጎት ደረጃ እንዳልኩህ ዛሬውኑ ቢያበቃልን ደስ ባለን፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን፣ የዓለም ጉዳይ ነው፡፡ ክትባት ተገኘለት ወይ ሲባል ጅምሮች መታየታቸው ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ የወረርሽኙ ሥርጭት አንድ ቦታ ላይ ደርሶ ሥጋት ወደማይሆንበት ደረጃ ቢደርስ፣ ሁሉም ዓለም የሚፈልገው ነገር ነው፡፡ በእኛ ሁኔታ በርካታ ትንበያዎች አሉ፡፡ አንዳንዶች ኅዳር ላይ ነው ወረርሽኙ ጫፍ ደርሶ የሚመለሰው የሚሉ ይኖራሉ፡፡ በአብዛኛው ምክንያታዊ የሆነው ዳሰሳ በክረምቱ እየተባባሰ ሊመጣ ይችላል የሚለው ነው፡፡ ይህም ቢሆን ግን መላምት ነው፡፡ በጣም አጽንኦት ልሰጥበት የምፈልገው ጉዳይ፣ እነዚህ ሁሉ የጠቀስናቸው ነገሮች መላምቶች ናቸው፡፡ በእርግጠኝነት በዚህ ጊዜ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በዚህ ጊዜ ይወርዳል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር የሚችል የለም፡፡ መጀመርያ ሰሞን የምንሠራው የበሽታው ሥርጭት ማሳያ ሰንጠረዥ በጣሊያን የታየውን ዓይነት የሚመስል ነበር፡፡ ሁሉም የጤና ባለሙያ የበሽታውን ሥርጭት የሚያሳይ ሰንጠረዥና ምሥል እየሠራ፣ በሦስት ሳምንት ውስጥ እዚህ ደረጃ ሊደርስ ይቻላል የሚል ግምት ሲያስቀምጥ ነበር፡፡ ወረርሽኙ በአፍሪካ ደረጃ የራሱን ባህሪ አሳይቷል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በአፍሪካ ያለውን ሁኔታ ዓይቶ አዲስ ትንበያ አውጥቷል፡፡ በፍላጎት ደረጃ ወዲያውኑ እንዲቆምልን እንፈልጋለን፡፡ ምክንያቱም የጀመርናቸው በርካታ የሪፎርም ሥራዎች አሉን፡፡ ከፊታችን ምርጫ ይጠብቀናል፡፡ ሐሳቦች ተጋፍተው ሕዝብ የሚመስለውን የሚመርጥበት ነገር ለመሥራት ጠንካራ ዝግጅት ነበር፡፡ እንደ ኢኮኖሚ ቡድኑ አባል በምርጫ ክርክር ውስጥ ለሕዝቡ ያለንን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የበላይነት አማራጭ ሐሳቦች ለማሳየትና በሕዝቡ ልብ ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ ትልቅ ፍላጎት ነበረን፡፡ እነዚህ ነገሮች ሲዘገዩብህ ያሳስብሃል፡፡ ግን ምን ማድረግ ትችላለህ? ባለበት ሁኔታ መሄድ ነው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ የሚያበቃበትን ቁርጥ ቀን እናውቃለን የሚሉትን አንስማቸው፡፡ ማንም ይህን አያውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ፖሊሲ ምላሾቻችሁ እንምጣ፡፡ ከቀረጥ ነፃ ሆነው እንዲገቡ የተፈቀዱ የምግብ ሸቀጦች አሉ፡፡ ፓስታ፣ ማካሮኒና ዱቄትን ጨምሮ ይህንን ዕድል እንዲያገኙ መደረጋቸው፣ በአገር ውስጥ የሚገኙ አምራቾች ላይ ከፍተኛ ሥጋትና ጫና ማሳደሩን የሚያሳስብ እሮሮ እናንተ ጋር ሳይመጣ አልቀረም፡፡ በአገር ውስጥ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ቫትን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ታክስ እየከፈሉ ባሉበት ወቅት፣ ከውጭ በነፃ እንዲገባ መፈቀዱ ትክክል አይደለም እያሉ ነው፡፡

ኢዮብ (ዶ/ር)፡- ለየትኛውም አስመጪ ይህንን አልፈቀድንም፡፡ ተናበን እየሠራን ነው፡፡ ማካሮኒና ፓስታ ከቀረጥ ነፃ ይግባ የሚል ነገር የለም፡፡ ፍራንኮ ቫሉታ ከሆነ እሱ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ በራሳቸው የውጭ ምንዛሪ ምርት እንዲያስገቡ የፈቀድነበት መንገድ አለ፡፡ በተለመደው የአገራችን የንግድ ሕግ የውጭ ኩባንያዎች በንግድ ውስጥ መሳተፍ አይችሉም፡፡ በተለየ ሁኔታ ግን የኢንቨስትመንት ቦርድ በፈቀደውና የገንዘብ ሚኒስቴርም በሰጠው መመርያ መሠረት፣ በፍራንኮ ቫሉታ እንዲገባ ፈቅደናል፡፡ ነገር ግን የታክስ ሥርዓቱ እንዳይዛነፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል፡፡ ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ የሚፈቀድላቸው አሉ፡፡ ለምሳሌ ስኳር የሚገባው በስኳር ኮርፖሬሽን አማካይነት ነው፡፡ የተወሰኑ የዘይት ምርቶች በድጎማ ለደሃው የኅብረተሰብ ክፍል የሚገዙ አሉ፡፡ ከዚህ ውጭ አቅርቦት እንዲጨምር ፈቀድን እንጂ የተለየ ድጋፍ አልሰጠንም፡፡ ድጋፍም አላደረግንም፡፡ ትኩረታችን የአገር ውስጥ ምርት ላይ ነው፡፡ እናንተም ሄዳችሁ ማየት እንደምትችሉት እያንዳንዱ ኩባንያ በዘርፍ ደረጃ ድጋፍ እየተደረገለትና የገቢ ንግዱ ብዙም እንዳይበረታታ እያደረግን ነው፡፡ ለምሳሌ የፕላስቲክ ፓይፕና መሰል ምርቶችን ለሚያመርቱ ተቋማት የጥሬ ምርት ግብዓት እንዲያገኙ በማስቻል፣ ከውጭ የሚመጣ ምርት እንዳይገባ የመደገፍ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ከዚህ ቀደም የምንሰጣቸው የቀረጥ ነፃና መሰል ማበረታቻዎች የተናበቡ አልነበሩም፡፡ በአንድ በኩል የገቢ ንግዱን እያበረታታ በሌላ በኩል የአገር ውስጥ አምራቹን እየጎዳው መደገፍ የማያስኬድ በመሆኑ፣ አምራቹ የተሻለ የታክስ ማበረታቻ እንዲያገኝና ያለቁ ምርቶች ሲገቡ ተጨማሪ ታክስ እንዲጣልባቸው በማድረግ የተናበበ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡

Related Articles

Latest Articles

Most Popular

google.com, pub-5833971792216939, DIRECT, f08c47fec0942fa0